Connect with us

ሀገር ዉስጥ

35ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ይከናወናል።

Published

on

featured
Photo: Social Media

“35ኛው የአፍሪካ ህብረት መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ይከናወናል።”

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አንባሳደ ዲና ሙፍቲ

ከአመት በፊት አሸባሪው የሕውኃት ቡድን በሰሜን እዝ ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ   መንግሥት ተገዶ ወደ ጦርነት ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡ ለአንድ ዓመት የቆየው  ጦርነቱ የበርካቶችን ሕይወት አጥፍቷል፣ አዛውንቶችን ያለ ጧሪ ህፃናትን ያለ አሳዳጊ አስቀርቷል፡፡ እረጅም ዓመት የተለፋባቸው እና  በርካታ ቢሊዮን ብሮች የፈሰሰባቸው የመሠረተ ልማቶች ወደ ፍርስራሽነት ተቀይረዋል፡፡

በዚህ ወቀት አሜሪካን እና መሰል የአውሮፖ አገራት ከእውነታው ፍፁም በራቀ መልኩ ለአሸባሪው ሕውኃት በመወገን በመንግሥት ላይ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና  ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

አንዳንድ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንም የአሸባሪው ሕውኃት አፈ ቀላጤ በመሆን የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ  የሚያወናብዱ መረጃዎችን ሲያሰራጩ ተስተውለዋል፡፡

አሜሪካን ጨምሮ በርካታ  የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን አገሪቱ ከዳር እስከ ዳር የጦር ቀጠና መሆንዋን የሚገልፁ መግለጫዎችን እና ዘገባዎችን በተደጋጋሚ ሲያሰራጩ ተስተውለዋል፡፡

መንግሥት ይህን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመቀልበስ ብሎም በአገሪቱ የተሻለ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን ለማሳየት የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ የዲፕሎማሲ ድሎች እየተመዘገቡ ይገኛሉ፡፡

ከሳምንት በኋላ 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ የጉባኤው በአዲስ አበባ መደረግ ቀደም ሲል በአሜሪካ እና አጋሯቿ ሲሰራጭ የነበረውን አዲስ አበባ ተከባለች መረጃ የሚያጣፋ ነው ያሉት የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተንታኙ አቶ ሀብታሙ ገብረ መድህን ናቸው፡፡

ሕብረቱ ስብሰባውን በአዲስ አበባ እንዲደረግ መወሰኑ ኢትዮጵያውያን ብሎም አፍሪካውያን ሲያከናውኑት የነበረው  የበቃ (#No More) ዘመቻ ፍሬ ለማፍራቱ አንድ ማሳያ  ነው ይላሉ፡፡

ሌላው አስተያየታቸውን የአዋሽ ሬድዮ የሰጡት የዓለም አቀፍ ግንኙነት አጥኚው  ዶ/ር ጌድዮን ጃለታ ሕብረቱ የስብሰባውን መቀመጫ  ወደ ሌላ አገር ቢያዞር ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ኪሳራ ይሆን  ነበር ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ሕብረት መመሥረት ያደረገችው አስተዋፅዖ ትልቅ እንደነበረ ያነሱት አጥኚው አፍሪካውያን ትላንት የተደረገላቸውን ድጋፍ  አስበው ከኢትዮጵያ ጎን መቆማቸው መንግሥት ትልቅ ድል እንዲያገኝ አድርጎታል ባይ ናቸው፡፡

በቅርቡ መንግሥት ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያለው ትውልደ ኢትዮጵያውን ወደ አገራቸው መግባታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ  በአገሪቱ ላይ የተፈጠረውን መጥፎ ገፅታ እንዳደሰው የገለጹት ዶ/ር ጌድዮን ሕብረቱ  ስብሰባውን በአዲስ አበባ ለማድረግ የወሰነው  ከዚሁ መነሻ መሆኑን አጥኚው አብራርተዋል፡፡

ሕብረቱ ስብሰባውን በአዲስ አበባ ለማድረግ መወሰኑ የኢትዮጵያን ሰለማዊነት ለዓለም ሕዝብ በግልፅ መንገር የሚችል ነው ይላሉ ዶ/ር ጌድዮን፡፡

ኢትዮጵያውያን ለውጭ ኃይል ዕድል ሳይሰጡ በአንድነት በመቆማቸው ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ጣልቃ የመግባት ሴራ ማክሸፍ ችለዋል የሚሉት አቶ ሀብታሙ በቅርቡ መንግሥት በሆደ ሰፊነት በማረሚያ ቤት የነበሩ ፖለቲከኞች መፍታቱ እና ለመደራደር ማሰቡ የአገሪቱን የዲፕሎማሲ አቅም ለማጠናከር እድል እንዳሚሰጠው አቶ ሀብታሙ  አብራርተዋል፡፡

በድርድሩ ልዩነቶቻችን በንግግር መፍታት ከቻልን እና ውስጣዊ አንድነታችንን ማጠናከር ከተቻለ የዲፕሎሲያዊ ጥንካሬያችን እየጨመረ ይመጣል ያሉት ተንታኙ በቅርቡ የሚደረገው አገር አቀፍ  ድርድር በጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ከሳምንት በኋላ 35ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚከናወን ያነሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አንባሳደር ዲና ሙፍቲ ስብሰባው መቀመጫውን በአዲስ አበባ ለማድረግ በርካታ ዲፕሎማሲያዊ ውጣ ወረዶች መታለፋቸውን አንስተዋል፡፡ አምባሳደሩ ኮቪድን ሽፋን በማድረግ ስብሰባው በአካል በአዲስ አበባ እንዳይደረግ ጫናዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ከአገራት መሪዎች እና ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ባደረገው  ተደጋጋሚ ውይይት  የህብረቱ ስብሰባው በአዲስ አበባ እንዲከናወን መወሰኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለአፍሪካውያን ስታደርገው የነበረው ገንቢ ሚና አሁን ለምታከናውነው የዲፕሎማሲ እንቅስቀሴ ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ መሆኑን ያነሱት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ  በዘንድሮ ስብሰባ አፍሪካውያን መሪዎች በምግብ ተደራሽነት ላይ ውይይት አንደሚያደርጉ ጠቁመው፡፡

ስብሰባው በአዲስ አበባ መከናወኑ ለከተማዋ የሆቴል ኢንዱስትሪ እና ትራንስፖርት እንቅስቃሴ መነቃቃት ይፈጥራል ያሉት ቃል አቀባዩ ከምንም በላይ ኢትዮጵያ ሰላማዊ እና ዓለማቀፍ ስብሰባዎችን የማከናወን አቅም እንዳላት ማሳያ ይሆናል ብለዋል፡፡

በመጭው ሳምንት የሚከናወነው 35ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባ የፓን አፍሪካኒዝም ስሜት ያጠናክራል ተብሎ እንደሚታሰብ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አንስተዋል፡፡

የዘገበው፡- ይስሃቅ አበበ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

ሀገር ዉስጥ

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ባሏቸው ግለሰቦችና አስመራቂ ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ ነው ።

Published

on

featured
Photo: Social Media

በኢትዮጵያ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ባሏቸው ግለሰቦችና አስመራቂ የትምህርት ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ገለጸ። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን የትምህርት ጥራትን ከመቆጣጠር ባሻገር የትምህርት ማስረጃ ትክክለኛነትን የማረጋገጥ ሥራን ያከናውናል። በዚህም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የተማሪዎቻቸውን ዝርዝር መረጃና የትምህርት ማስረጃ ከምዝገባ እስከ ምረቃ ድረስ ለባለሥልጣኑ የመላክ ግዴታ አለባቸው።

ይህንንም ተከትሎ የትምህርትና ሥልጠና ባለሥልጣን ከ1995 ጀምሮ እስከ 2014 ዓ.ም መረጃቸውን ለተቋሙ ካስገቡ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ክትትል አድርጓል። በእነዚህ ተቋማት እስካሁን ከተመረቁ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ተማሪዎች መካከል ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የያዙ መሆኑን ነው የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዱዓለም አድማሴ እንደገለፁት ።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃውን የያዙት ግለሰቦች የብቃት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው፤ በ10+1 እና በ10+2 የዲግሪ የምስክር ወረቀት ከማግኘት እስከ እውቅና በሌለው የትምህርት መስክ እስከተመረቁ ይገኙበታል ነው ያሉት። እርምጃ መውሰድ ቢጀመር አንዳንድ ክልሎች ቢሮዎቻቸው ሊዘጉ ይችላሉ ያሉት ዶክተር አንዱዓለም፤ በአስመራቂ ተቋማትና የሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃው ባለቤቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝርዝር ማጣራት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከት ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ባለሥልጣኑ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የሰጡ ተቋማትን በሕገ-ወጥ መንገድ ዲግሪ ያገኙ ተመራቂዎችን ለማጋለጥ ወደ ኋላ እንደማይልም ነው የተናገሩት። እንደ አገር መወሰድ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ መንግሥት አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ የተለያዩ የውሳኔ ሐሳቦችን በማካተት እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

ለ20 ዓመታት የተንከባለሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከል እየሞከርን ነው” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የተመራቂዎቻቸውን ሙሉ መረጃ እንዲልኩ የማድረግ ሥራ ይከናወናል ብለዋል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ129 ከተሞች ከ2 ሺህ 500 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍተው ከ3 ሺህ 315 በላይ የትምህርት መርሃ-ግብሮችን በማስተማር ላይ ናቸው።

Continue Reading

ሀገር ዉስጥ

የመቀንጨር አደጋ የተጋረጠበት በርካታ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በስፋት እንደሚገኝ ጥናቶች ያመላክታሉ።

Published

on

featured
Photo: Social Media

ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ቁጥር መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዘው ማህበረሰብ በግብርና እንደሚተዳደር ይታወቃል።የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ ፖሊሲም እስከቅርብ አመታት ድረስ ግብርና መር እንዲሆን ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል። ይሁን እንጂ እስካሁን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ አለመቻሉን ለምን የሚያስብል ጉዳይ ነው። የምግብ ዋስትናን ካለማረጋገጥ ባለፈ በተለይ በገጠር የሚኖረውን ማህበረሰብ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለበት ይታወቃል።

በመሆኑም አሁንም ድረስ እንደሀገር የመቀንጨር አደጋ የተጋረጠበት በርካታ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በስፋት እንደሚገኝ ጥናቶች ያመላክታሉ። ይህ ደግሞ የትምህርት መዛባትን የጤናማ እና ብቁ ዜጋን ሊያሳጣ እንደሚችል ይገለፃል። የተጋረጠውን ሀገራዊ ችግር ለመቅረፍ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ምን እየሰሩ ነው እንደ ሀገር የመቀንጨር አደጋ ምጣኔያችንስ ምን ያክል ደርሷል ስንል ባለሙያዎችን አነጋግረናል።

በኢትዮጵያ ከሁለት አመት በፊት በተደረገ ጥናት የመቀንጨር አደጋ 37 በመቶ የደረሰ ምጣኔ አለው። ይህ የመቀንጨር አደጋ በስፋት የሚታየው የ 6 ወር እስከ 59 ወር ያሉ ህፃናት ላይ ሲሆን እንደ ሀገር ከ6 ሚሊየን በላይ ከ5 አመት በታች ያሉ ህፃናት የመቀንጨር አደጋ አጋጥሟቸዋል ሲሉ በሰቆጣ ቃልኪዳን የፌዴራል ፕሮግራም ማስፈፀሚያ ዋና ሀላፊ ዶክተር ሲሳይ ሲናሞ ይናገራሉ። የመቀንጨር አደጋ እንደሀገር በጤና ላይ በትምህርት ላይ እና በሀገር ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ቀውስ ስለሚያስከትል ይህን ለመቅረፍ የሰቆጣ ቃልኪዳን ተቀርፆ እየተሰራ ነው ሲሉ ዶክተር ሲሳይ ሲናም ያክላሉ።

በሀገራችን የምግብና ስርዓተ ምግብ ችግር እንደሀገር ካሉ ቁልፍ ችግሮች መካከል አንደኛው እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ። በሀገር ውስጥ የሚከሰቱ ተፈጥሮዋዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ደግሞ ይበልጥ ችግሩን ከፍ ሊያደርጉት እንደሚችሉ ይታወቃል። ይህን ችግር ለመፍታት ግን ዘለቂታዊነት ያለው የምግብና የአመጋገብ መመሪያና ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ የጤና ሚኒስቴር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገልፀዋል። ምግብ አጠር በሆኑ አከባቢዎች ላይ እየተከሰተ የሚገኘው የመቀንጨር ችግር እንደሀገር በሰው ሀብት ልማት ላይ ተፅዕኖ ከመፍጠር ባለፍ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ውጤታቸው አነስተኛ እንዲሆኑ እያደረገ ነው በማለት የትምህርት ሚኒስቴር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ተናግረዋል።

ትምህርት ሚኒስትርም የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የአመጋገብ ስርዓትን በመማርማስተማር ስርዓቱ ውስጥ ከመቅረፅ በተጨማሪ አዲስ በሚገነቡ ትምህርት ቤቶች ላይ የተመጣጥጠነ ምግብ ሊመረተባቸው የሚችሉ የእርሻ ቦታዎች በትምህርት ቤቶች እንዲዘጋጁ እየተደረገ ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ይጨምራሉ። በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክኒያት የሚፈጠሩ ችግሮችን በዋነኝነት ለመፍታት የግብርናው ዘርፍ ሚናው ያልቀ በመሆ የግብርና ሚኒስቴርም የተመጣጠነ ምግብ እንደሀገር ተደራሽ ለማድረግ በቴክኖሎጊ የታገዘ ዘመናዊ የአመራረት ዘይቤን መከተል ስለሚያስፈልግ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ አሰራሮች ተነድፈው ወደ ተግባር እየተገነባ ነው በማለት የግብርና ሚኒቴር ድኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ገልፀዋል።

በምግብ እጥረት ምክኒያት የሚመጡ ሀገራዊ ችግሮች ከፍታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ የመፍትሄ ሂደታቸው ከአንድ አቅጣጫ እንደማይመጣ ይታወቃል በመሆኑም ችግሩን ለመቅረፍ የተቀናጀ አሰራር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።
በዮሃንስ አበበ

Continue Reading

ሀገር ዉስጥ

በባለሙያ የታገዘ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እና የተፍጥሮ ሀብት ላይ መሰረት አድርጎ መስራት አማራጭ የሌለዉ ነዉ።

Published

on

featured
Photo: bloomberg, women sitting in a market

በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት ከዛሬ ነገ መፍትሄ ይገኝለታል ተብሎ ቢጠበቅም ይበልጥ እየናረ እየናረ መቷል ። በእለት ከእለት ጠቀሜታ ላይ የሚውሉ የኢንዱስትሪ ምርቶች በአንዴ ከ 2 መቶ እስከ 4 መቶ ብር በላይ ጭማሪ ማሳየት መጀመራቸው ደግሞ ድንጋጤን እየፈጠረ ይገኛል ።
ችግሩን ደግሞ አስገራሚ የሚያደርገው የምርት ጥሬ እቃቸው ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በብዛት ማቅረብ የሚቻልባቸው ምርቶች መሆናቸው ተጠቃሚው ማህበረሰብ ለምን የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል ።
ኢትዮጵያ በስፋት የምታመርታቸው የቅባት እህል ምርቶች የሀገር ውስጥ ፍጆታን የመሸፈን አቅም እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቢደመጥም እንደ ዘይት እና መሰል ምርቶችግን ዋጋቸው ጣራ እየነካ ይገኛል።
እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬ በስፋት ከሚገኝባቸው ምርቶች መካከልም ይሄው የቅባት እህሎች መሆናቸው ለውጭ ፍጆታ የሚቀርቡት የሀገር ውስጥ ፍጆታን በቅድሚያ ሳይሸፍኑ ነው ወይ የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሳ ያደርጋል ።

አዋሽ ሬድዮም ለውጭ የሚላኩ ምርቶች ሳይቀንሱ በምን አይነት መንገድ ቢሰራ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ማሟላት ይቻላል የሚታየውን ንረት ለማረጋጋት የሀገር ውስጥ ምርቶቻችን ላይ ምን ሊሰራ ይገባል ስንል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግረናል ። በአለም አቀፍም ሆነ በሀገር ዉስጥ ያለዉ የንግድ ፖሊሲ የተስተካከለ አለመሆኑ ለኢንድስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶች በሀገር ዉስጥ እያሉን ምርቱን ኮዉጭ ለማስገባት እየተገደድን ስለሆነ ችግሮች በአለም አቀፍ ደረጃ ሲከሰቱ እኛም አብረን እንድንቸገር ተደርገናል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ያሬድ ሀይለመስቀል ይገልፃሉ ፡፡

አሁን ያለዉን የኑሮ ዉድነት ችግር ለመፍታት እና የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲስተካከል መንግስት የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዉን እንደገና በባለሙያዎች ማስተካከያ ሊያደርግበት ይገባል ፡፡
በተጨማሪም ያለንን የተፈጥሮ ሀብት የምንጠቀምበትም መንገድ ሊመቻች ይገባል ሲሉ አቶ ያሬድ ይጨምራሉ ፡፡

በሀገር ዉስጥ በስፋት የምናመርተዉን የቅባት እህል እንኳን ሙሉ ለመሉ በሚባል ደረጃ ወደ ዉጭ በመላክ በምትኩ ለዘይት ማምረቻ የሚሆን ግብአት እያስገባን እንገኛለን ፡፡
ይህ በመሆኑ በዘይትም ሆነ በሌሎች መሰል ምርቶች ላይ የሀገር ዉስጥ አምራቾች ከገበያ እንዲወጡ በመደረጋቸዉ የዋጋም ንረት እና ሆነ የምጣኔ ሀብት ድቀት አድርሶብናል ያሉት ደግሞ ሌላኛዉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ደምስ ጫን ያለዉ ናቸዉ ፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ላይ እጅግ የጨመረዉ የዘይት ምርትን እንኳን ብናነሳ ከ ሁለት አስርት አመታት በፊት ተግባራዊ በተደረገዉ የፓልም ዘይት የቀረጥ ነፃ ማስገባት የግብይት አሰራር በዘርፋ ተሰማርተዉ የነበሩ አምራቾች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ፡፡ በሌሎች ዘርፍም የሆነዉ ይህን መሰል አሰራር በመሆኑ ጥሬ ግብአት ወደ ዉጭ ልከን የተቀነባበረ እያስገባን በመሆኑ ላልተገባ ወጭ እየተዳረግን ነዉ ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ ዶክተር ቆስጠንጢኒዮስ በርኸ ተስፋ ይገልፃሉ ፡፡

ወደዉጭ ገበያ የምናቀርባቸዉ የሀገር ዉስጥ ምርቶች አብዛኛዎቹ ጥሬ ምርቶች በመሆናቸዉ ከምናገኘዉ ጥቅም ይልቅ የምናጣዉ ያመዝናል ፡፡ በመሆኑም ጥሬ የግብርና ምርቶችን ለዉጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ የተቀነባበረ ምርት ማቅረብ ብንጀምር የምናገኘዉንም የዉጭ ምንዛሬ መጨመር እንችላለን በተጨማሪም ከዉጭ የምናስገባቸዉን የኢንዲስትሪ ግብአት እዚሁ በሀገራችን ማምረት የምንችልበት እድል ልናገኝ እንችላለን በማለት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ሳለ አምላክ ዘላለም ሀሳባቸዉን አንስተዋል ፡፡

እያናረ የሚገኘዉን የኑሮ ዉድነት እና እየወደቀ የሚገኘዉን የሀገርን ምጣኔ ሀብት እንዲያገግም ዋነኛ አማራጭ የሚሆነዉ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በተገቢዉ ሁኔታ መጠቀም ግዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነዉ ሲሉ ዶክተር ቆስጠንጢኒዮስ ተናግረዋል ፡፡

የበርካታ ዜጎች እራስ ምታት የሆነዉን የኑሮ ዉድነት እና የምጣኔ ሀብት ድቀት ለማሻሻል በአፋጣንኝ በባለሙያ የታገዘ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እና የተፍጥሮ ሀብት ላይ መሰረት ያደረጉ ስራዎችን መስራት አማራጭ የሌለዉ ጉዳይ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል ፡፡

በዮሃንስ አበበ

Continue Reading

በብዛት የተነበቡ