በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት ከዛሬ ነገ መፍትሄ ይገኝለታል ተብሎ ቢጠበቅም ይበልጥ እየናረ እየናረ መቷል ። በእለት ከእለት ጠቀሜታ ላይ የሚውሉ የኢንዱስትሪ ምርቶች በአንዴ ከ 2 መቶ እስከ 4 መቶ ብር በላይ ጭማሪ ማሳየት መጀመራቸው ደግሞ ድንጋጤን እየፈጠረ ይገኛል ።
ችግሩን ደግሞ አስገራሚ የሚያደርገው የምርት ጥሬ እቃቸው ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በብዛት ማቅረብ የሚቻልባቸው ምርቶች መሆናቸው ተጠቃሚው ማህበረሰብ ለምን የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኗል ።
ኢትዮጵያ በስፋት የምታመርታቸው የቅባት እህል ምርቶች የሀገር ውስጥ ፍጆታን የመሸፈን አቅም እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቢደመጥም እንደ ዘይት እና መሰል ምርቶችግን ዋጋቸው ጣራ እየነካ ይገኛል።
እንደ ሀገር የውጭ ምንዛሬ በስፋት ከሚገኝባቸው ምርቶች መካከልም ይሄው የቅባት እህሎች መሆናቸው ለውጭ ፍጆታ የሚቀርቡት የሀገር ውስጥ ፍጆታን በቅድሚያ ሳይሸፍኑ ነው ወይ የሚሉ ጥያቄዎች እንዲነሳ ያደርጋል ።
አዋሽ ሬድዮም ለውጭ የሚላኩ ምርቶች ሳይቀንሱ በምን አይነት መንገድ ቢሰራ የሀገር ውስጥ ፍጆታን ማሟላት ይቻላል የሚታየውን ንረት ለማረጋጋት የሀገር ውስጥ ምርቶቻችን ላይ ምን ሊሰራ ይገባል ስንል የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችን አነጋግረናል ። በአለም አቀፍም ሆነ በሀገር ዉስጥ ያለዉ የንግድ ፖሊሲ የተስተካከለ አለመሆኑ ለኢንድስትሪ ግብአት የሚሆኑ ምርቶች በሀገር ዉስጥ እያሉን ምርቱን ኮዉጭ ለማስገባት እየተገደድን ስለሆነ ችግሮች በአለም አቀፍ ደረጃ ሲከሰቱ እኛም አብረን እንድንቸገር ተደርገናል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ያሬድ ሀይለመስቀል ይገልፃሉ ፡፡
አሁን ያለዉን የኑሮ ዉድነት ችግር ለመፍታት እና የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት እንዲስተካከል መንግስት የምጣኔ ሀብት ፖሊሲዉን እንደገና በባለሙያዎች ማስተካከያ ሊያደርግበት ይገባል ፡፡
በተጨማሪም ያለንን የተፈጥሮ ሀብት የምንጠቀምበትም መንገድ ሊመቻች ይገባል ሲሉ አቶ ያሬድ ይጨምራሉ ፡፡
በሀገር ዉስጥ በስፋት የምናመርተዉን የቅባት እህል እንኳን ሙሉ ለመሉ በሚባል ደረጃ ወደ ዉጭ በመላክ በምትኩ ለዘይት ማምረቻ የሚሆን ግብአት እያስገባን እንገኛለን ፡፡
ይህ በመሆኑ በዘይትም ሆነ በሌሎች መሰል ምርቶች ላይ የሀገር ዉስጥ አምራቾች ከገበያ እንዲወጡ በመደረጋቸዉ የዋጋም ንረት እና ሆነ የምጣኔ ሀብት ድቀት አድርሶብናል ያሉት ደግሞ ሌላኛዉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ደምስ ጫን ያለዉ ናቸዉ ፡፡
በኢትዮጵያ አሁን ላይ እጅግ የጨመረዉ የዘይት ምርትን እንኳን ብናነሳ ከ ሁለት አስርት አመታት በፊት ተግባራዊ በተደረገዉ የፓልም ዘይት የቀረጥ ነፃ ማስገባት የግብይት አሰራር በዘርፋ ተሰማርተዉ የነበሩ አምራቾች ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል ፡፡ በሌሎች ዘርፍም የሆነዉ ይህን መሰል አሰራር በመሆኑ ጥሬ ግብአት ወደ ዉጭ ልከን የተቀነባበረ እያስገባን በመሆኑ ላልተገባ ወጭ እየተዳረግን ነዉ ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ ዶክተር ቆስጠንጢኒዮስ በርኸ ተስፋ ይገልፃሉ ፡፡
ወደዉጭ ገበያ የምናቀርባቸዉ የሀገር ዉስጥ ምርቶች አብዛኛዎቹ ጥሬ ምርቶች በመሆናቸዉ ከምናገኘዉ ጥቅም ይልቅ የምናጣዉ ያመዝናል ፡፡ በመሆኑም ጥሬ የግብርና ምርቶችን ለዉጭ ገበያ ከማቅረብ ይልቅ የተቀነባበረ ምርት ማቅረብ ብንጀምር የምናገኘዉንም የዉጭ ምንዛሬ መጨመር እንችላለን በተጨማሪም ከዉጭ የምናስገባቸዉን የኢንዲስትሪ ግብአት እዚሁ በሀገራችን ማምረት የምንችልበት እድል ልናገኝ እንችላለን በማለት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዉ አቶ ሳለ አምላክ ዘላለም ሀሳባቸዉን አንስተዋል ፡፡
እያናረ የሚገኘዉን የኑሮ ዉድነት እና እየወደቀ የሚገኘዉን የሀገርን ምጣኔ ሀብት እንዲያገግም ዋነኛ አማራጭ የሚሆነዉ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት በተገቢዉ ሁኔታ መጠቀም ግዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነዉ ሲሉ ዶክተር ቆስጠንጢኒዮስ ተናግረዋል ፡፡
የበርካታ ዜጎች እራስ ምታት የሆነዉን የኑሮ ዉድነት እና የምጣኔ ሀብት ድቀት ለማሻሻል በአፋጣንኝ በባለሙያ የታገዘ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እና የተፍጥሮ ሀብት ላይ መሰረት ያደረጉ ስራዎችን መስራት አማራጭ የሌለዉ ጉዳይ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል ፡፡
በዮሃንስ አበበ