በኢትዮጵያ 80 በመቶ የሚሆነዉ ማኅበረሰብ በግብርና ምርት ላይ የተሰማራ እንደሆነ ይሚታወቅ ነው፡፡ የዘርፉ አጥኚዎች እንደሚናገሩት በኢትዮጵያ በግብርና የሚተዳደር የህዝብ ቁጥር ብቻ ብዛት ሳይሆን ሊታረስ የሚችል ምቹ የሆነ ለም መሬትና ለየትኛውን ምርቶች የሚያስፈልግ የአየር ንብረት እንዳለ ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን እስካሁንም ድረስ የሚሰራበት በኋላ ቀር የአሰራር ሂደት በመሆኑ መሠረታዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት አይደለም ለዓመት የሚበቃ የምግብ አቅርቦትም ማምረት አልቻልንም ሲሉ ይገልፃሉ፡፡ ይህን ለማስተካከል በዋናነት የተለያዩ ምርጥ ዘሮችን ከመጠቀም ባለፈ የሰለጠነ የሰው ኃይል በዘርፉ ሊኖር እንደሚገባ ሲነገር ይደመጣል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ግብርና መር ላይ ትኩረት ያደረጉ የትምህርት ዘርፎችን በዘመናዊ መንገድ ለማስተማር ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለባቸው አስረግጠው ሙሁራኑ ይናገራሉ፡፡
በዚህ መልኩ የሰለጠነና በዘመናዊ መንገድ የታገዘ ግብርና መር ኢንዱስትሪን መፍጠር ካልቻልን የግብርና ምርቶችም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች የዋጋ ንረት ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይስተዋልም፡፡ በተለይ ባለፉት ተከታታይ አስር አመታት የኑሮ ዉድነቱ እያሻቀበ መምጣቱ አብዛኛዉን ማህበረሰብ እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚነሳው ህገ-ወጥ የንግድ ትስስር መኖሩ እንደሆነ በርካቶች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡
በተለያዩ ወቅቶችም በህገ-ወጥ ነገጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አና እየተወሰደ እንዳለ ቢነገርም የኑሮ ውድነቱ ሰጨምር እንጅ ሲቀንስ አልተስተዋልም፡፡ ይህንን በርካቶችን እረፍት የነሳ የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ ሲባልም የተለያዩ ድጎማዎች ቢደረጉም ለውጦች ግን እብዛም እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የፌደራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲም የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ የሚያስችል ዐውደ ርዕይ እና ባዛር በትላንትናው እለት መጀመሩ ተሰምቷል፡፡
አዋሽ ሬዮም የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲን አናግሮ ጉዳዩን ተመልክቶታል :: የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ከትላንት ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ዐውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ማስጀመሩ ተገልጿል፡፡
በዚህ ዐውደ ርዕይ ላይ 138 የሚደርሱ የኅብረት ስራ ማኅበራት እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን 38 የሚደርሱ ደግሞ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ድርጅቶች ይሳተፋሉ ሲሉ የፌደራል ኅብረት ስራ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አያልሰዉ ወርቅህ ገልፀዋል፡፡
በዐውደ ርዕዩ ላይ ባለው ሀገራዊ ችግር ምክንያት ከትግራይ ክልል ዉጭ ሀሉም ክልሎች ምርትና አገልግሎታቸዉን ይዘዉ ለተጠቃሚ ቀርበዋል ሰሉ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡ በፕሮግራሙ ከ82 በላይ የግብርና ምርቶች ለግብይት ይቀርባሉ ተባለ ሲሆን በአብዛኛው ኅብረተሰቡ በእለት ከእለት የሚጠቀምባቸዉው የፍጆታ ምርቶች ትኩረት ተሰቷቸዋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የኅብረት ስራ ማህበራት በራሳቸው ያመረቷቸው የፋብሪካ ዉጤቶች ለግብይት በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርበዋል ተብሏል፡፡ እንደዚህ አይነት መሰል ዐውደ ርዕይ መዘጋጀታቸው ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን ምርት በተወሰነ ቦታ በሚፈልገዉ መጠንና ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ እንደሚረዳው ተገልጿል፡፡
ይህንንም ለማስቀጠል ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች ክልሎችም መሰል ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፤ ለማድረግም እየተዘጋጁ ያሉ ክልሎች አሉ የተባለ ሲሆን የግብይት ፕሮግራሞቹ በዋናነት አምራችን ከትክክለኛዉ ሸማች ጋር እንደሚያገናኙ ተነግሯል፡፡
በዮሐንስ አበበ