በእስልምና እምነት ውስጥ በዓመት የሚከበሩ ሁለት ትላልቅ ክብረ በዓላት ያሉ ሲሆን ኢድ አል አድሀ (አረፋ) እና ኢድ አልፈጥር በመባል ይታዋቃሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የአረፋ በዓል አከባበር ስንመለከት በእስልምና አምስቱ መሰረቶች አንዱ ከሆነው ከሀጅ ስነ-ስርዓት (የአላህን ቤት ከመዘየር) ጋር የተያያዘ ሲሆን የበዓሉ ስም በእስልማና ታሪክ ትልቅ ቦታ ካለው ከአረፋ ተራራ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ማለትም የአረፋ ተራራ በመካ አካባቢ ከሚገኙት ተራሮች አንዱ ሲሆን አባታችን አደምና ሃዋ አሏህ እንዳይበሉት ከልክሎአቸው የነበረው ዘር በመብላታቸው አሏህ ተቆጥቶባቸው ከነበሩበት የጀነት ዓለም አስወጥቶ ወደ ምድር ካመጣቸው በኋላ ለብዙ ዘመናት እንዳይገናኙ አራርቆ ካኖራቸው በኋላ አሏህ ታርቆቸው እንዲገናኙ በመፍቀዱ የተገናኙበት ስፍራ (ተራራ) ነው፡፡
በአረፋ ወቅት ከሚከናወኑት ሀይማኖታዊ ተግባራት ውስጥ ዋናዎቹ የሐጅ ስርዓት ማከናወን(ካዕባን) መዘየርና መጠወፍ እንዲሁም ኡዱህያ(ዕርድ) ማድረግ ናቸው፡፡ ኡድህያ(ዕርድ) የሚከናውንበት ምክንያት አሏህ ነብዩላህ ኢብራሂምን ልጃቸው ኢስማኤልን እንዲያርዱት አዝዞአቸው የአሏህን ትዕዛዝ ያለምንም ማመንታት ለመፈጸም ልጃቸውን ለእርድ ሲያዘጋጁ ጅብሪል (አ.ሰ) ከጀነት በግ አምጥቶ እንዲቀይርላቸው ታዘዘ፡፡ ልጁ ሳይታረድ በመቅረቱና አባታችን አደም ከእናታችን ሃዋ ጋር ለብዙ ዘመናት በምድር ላይ ተለያይተው ከኖሩ በኋላ አሏህ እንዲገናኙ በመፍቀዱ ምክንያት የደስታ በዓል ሆኖ በየአመቱ እንዲከበር አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት የአረፋ በዓልና የእርድ ስነ-ስርዓት በእስልማና ህግ አንድ በሬ ለሰባት ሰው የሚታረድ ሲሆን የሚታረደው በሬ የተሟላ አካልና ጤናማ ሊሆን ይገባል፡፡ ሌላው አንድ ሰው ካስገባው የቅርጫ ስጋ 1/3 ኛው ለድሃ 1/3ኛው ከጎረቤትና ቤተዘመድ 1/3ኛው ለቤተሰቡ አካፍሎ እንዲጠቀም ሀይማኖታዊ አስተምሮው ያዛል፡፡ ይህ የመተሳሰብና የመረዳዳት ሃይማኖታዊ እሴት በባዓል ወቅት መደረጉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አባቶች ያስረዳሉ፡፡ የእርዱም ስነ ስርዓት የሚከናወነው በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከናወነው የዒድ ሶላት ከተከናወነ በሀዋላ ፈጣሪን በማመስገን ለሀገር ልማትና እድገት ሰላም እንዲሁም ድህነትን አስመልክቶ ዱአና ምርቃት በማድረግ አባወራዎችና ወጣቶች በተገኙበት ይካሄዳል፡፡
በሁሉም የሃገሪቱ ክፍል የአረፋ በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት በድምቀት ይከበራል፡፡ ለበዓሉ የሚደረገው ዝግጅት በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብለው ባሉት ወራቶች ውስጥ የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሰረት እናቶች ለበዓሉ ማድመቂያ የሚሆኑ ቤት እንዳፈራው ያዘጋጃሉ፣ ሴቶች ልጆቻቸው ደግሞ የመኖሪያ ቤቶችን በማስዋብ፣ የመመገቢያ ቁሶችን በማጽዳትና ሌሎች ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ቅድመ መሰናዶዎችን በማሟላት ስራ ይጠመዳሉ፡፡ ልክ እንደ ሴቶቹ ሁሉ ወንዶቹም ለአረፋ በዓል የሚያከናውኗቸው የስራ ድርሻ አላቸው፡፡ ለማገዶ የሚሆን እንጨት ፈልጦ ማዘጋጀት፣ ለእርድ የሚሆን ከብት ማቅረብ በአባቶችና በወንድ ልጆቻቸው የሚከወን ይሆናል፡፡ በመሆኑም የአረፋ በዓል በስራ ምክንያት ተራርቆ የቆየውንም ሙስሊም ቤተሰብ ከያሉበት አሰባስቦ የሚያገናኝም በዓል ነው ለማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአረፋ በዓል ቀደም ሲል ተጫጭተው የቆዩ የሚሞሸሩበት፣ ሌሎች ትዳር ለመመስረት የትዳር ጓደኛቸውን የሚመርጡበትና በባህሉ መሰረት የሚያጩበትም ጭምር መሆኑን የእምነቱ ተከታይ አባቶች ያስረዳሉ፡፡
ሌላው የአረፋ በዓል ያለው ማህበራዊ ፋይዳ በተጣሉ ሰዎች መሀል እርቀና ሰላም እንዲወርድ የሚያስችል ሃይል እንዳለው ሃይማኖታዊ አስተምሮቶች ያስረዳሉ፡፡ ከበዓሉ በፊት የተቀያየሙ ባልና ሚስት፣ልጅና ወላጅ፣ ጎረቤታሞች እንዲሁም የአንድ ማህበረሰብ ጎሳዎች በተፈጠሩ ያለመግባባቶች ያሉ ችግሮችን በአረፋ ሰሞን “ይቅር” ተባብለው ሰላምን ያወርዳሉ፡፡ ይህ ከተከናወነ በሀዋላ ለበዓሉ የተዘጋጁትን ምግብና መጠጥ አብረው በመብላትና በመጠጣት ይደሰታሉ፡፡ የቤተሰብ ህይወት እንዲሻሻል ምንመደረግ አለበት? የሃገሪቷ ሰላም እንዲሰፍንና በአካባቢው ልማት እንዲስፋፋ በአንድነት ከቤተሰብ እና ከማህበረሰቡ ጋር ይመክራሉ፡፡ የአረፋ በዓል ሙስሊም በሆነው ምእመናን ዘንድ ሁሉ ከፍተኛ ግምት ሰጥቶት የሚከበር በዓል ሲሆን ከመብላትና መጠጣቱ ባሻገር ሌሎች በርከት ያሉ ቤተሰባዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች ጭምር ያሉት እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአንዳን አካባቢዎች የእምነቱ አስተምህሮ ባይሆንም የሴቶች አረፋ እየተባለ ከዋናው የዒድ በዓል ዋዜማ የሚከበር በዓል አለ። በዚህ እለት ሴቶች የበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የሚያረጋግጡበት ቀን ነው፡፡
በዳኛቸዉ መላኩ