የሱዳን የባላደራ መንግስት የሱዳንን ህዝባዊ ቁጣ ያበርደዉ ይሆን? የአሜሪካ አቋምስ ምንድነዉ?
አልቡርሓን ሰሞኑን ድንገተኛ በተባለለት ሁኔታ የተወሰኑ ሚኒስተሮችንና ሌሎች ባለስልጣናት በማደራጀት ጊዚያዊ መንግስት ወይም ባላደራ መንግስት ማቋቋማቸዉን ተከትሎ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነዉ።
የባለ አደራዉን መንግስት ተከትሎ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ የአሜሪካ መንግስት እና የሱዳን መንግስት በጋራ በሰጡት መግለጫ የአሜሪካ መንግሰት እንደደገፈዉ በመግለፅ ላይ ናቸዉ።
ሱዳናዊያን ምሁራን ግን ይህን ሓሳብ አይጋሩትም እንዲያዉም የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤትና ወታደራዊዉ ክንፍ ሆነዉ መግለጫ መስጠታቸዉ የሚያሳየን ኘገር ቢኖር ሁለቱ አካላት ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያሳዩት የንቀት መለኪያ ነዉ ሲሉ ይደመድማሉ።
አል ቡርሓን መፈንቀለ መንግስቱን አድርገዉ ሱዳን በርካታ ዉስብስብ ነገሮችን ባሳለፈ በሁለተኛ ወሩ 15 አባላትን ያካተተ የሚኒስትሮች ቡድን ያቋቋሙ ሲሆን እነዚህ አባላት በባላደራነት ሱዳንን ያሻግራሉ የተባሉ ናቸዉ።
የሱዳን ህገ መንግስት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ወሳኝ ነዉ በሚል እነዚህ አዲስ ተሿሚዎች ሱዳንን እስከ ምርጫዉ ድረስ እያስታመሙ ይመሩታል እየተባለም ነዉ።
ግን እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸዉ በርካታ ጥያቄዎች አሉ ከእነዚህ መካከል እንደ እሳት ወላፈን የሚያቃጥለዉን ተቃዉሞ ማስቆም ይችላሉ ወይ? ሱዳንን እየፈተነ ያለዉን የኢኮኖሚ ቀዉስ ማስተካከል ይችላሉ ወይ? ጣራ የነካዉን የኑሮ ዉድነቱንስ ማዉረድ ይችላሉ ወይ? በፋብሪካዎች መዘጋት ሳቢያ ሱዳን ዉስጥ የተንሰራፋዉን የስራ አጠሰነት ቁጠሰር መቀነስ ይችላሉ ወይ? የሚሉትን ማንሳት ይቻላል።
የኢኮኖሚ ጉዳዮች ኤክስፐርት የሆኑት ዶር ዓብዱልዓዚም አልሙሐል በዚህ ጉዳይ ሰፋ ያለ አስተያየት ከሰጡት ምሁራን መካከል አንዱ ናቸዉ።
እንደእርሳቸው አገላለፅ ከሆነ ይኸ የባለአደራ መንግስት ስራ ከመጀመሩ በፊት ከወታደራዊዉ ክንፍ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተፅእኖ ራሱን ያፀዳ መሆኑን ለሱዳን ህዝብ ማሳየት አለበት ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ ዶ/ር ዓብዱልዓዚም አልሙሐል ከሆነ ይኸ አሁን የተቋቋመዉ የባላደራ መንግስት ሱዳን ዉስጥ መፍትሔ ካጣዉ የፓለቲካ ፉክክር መሳሳብ እና መናቆር ራሱን ማግለል መቻል አለበት ብለዋል።
የባላደራዉ መንግስት ዋነኛ ዓላማ ጣራ ከቀን ወደ ቀን እየናረ የመጣዉን የዶላር ምንዛሬ ማስተካከል ይኖርባቸዋል ይህን ማድረግ ካልቻሉ በእጥፍ የጨመሩትን የፍጆታ እቃዎች ዋጋ መቀነስ አይችሉም ያሉት ዶር አብዱልዓዚም የእነሱ ስራ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ እንጅ ፖለቲካዉ አይመለከታቸዉም።
እኔ በበኩሌ ይላሉ ዶር ዓብዱልዓዚም እኔ በበኩሌ የምመርጠዉ ለእነዚህ አዲስ ተመራጭ ባላደራዎች ከባድና ዉስብስብ ሓላፊነት ባይጣልባቸዉ ጥሩ ነዉ ቀለል ያሉ የተቆጠሩ የሚመዘኑ የማህበረሰቡን መሰረታዊ ችግሮች ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ ጥቂት ነገሮች ቢሆኑ እመርጣለሁ ይላሉ ዶር ዓብዱልዓዚም።
እዉቁ ሱዳናዊ የፖለቲካ ተንታኝ ጀማል ሮስቶም በበኩሉ የባላደራዉ መንግስት ሱዳን ባልተረጋጋበት እና ዉስብስብ ችግሮች ባሉበት ወቅት እንደመጣ መንግስት ብዙ ፈተናዎች አሉበት ።
ሱዳን ዉስጥ ፖለቲካዉ የሚመራበት ሰነድ የለም፣ ፓርላማ የለም፣ መንግስት ዉስጥ የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ የለም፣ ሱዳን ዉስጥ እርስ በርስ መተማመን የለም፣ መጠላለፍ እንጅ መደጋገፍ የለም ስለሆነም በዚህ ወቅት ሱዳንን ለማሻገር መሞከር በመርፌ ቀዳዳ እንደ መሹለክ ነዉ።
ከአሰነዚህ ከላይ ከጠቀስናቸዉ ችግሮች በበለጠ ወጣቱ ጠንካራ ጥያቄዎች አሉት ከሁሉም በፊት የወጣቱን ጥያቄ መረዳትና መመለስ ያስፈልጋል።
የባለአደራዉን መንግስት አልቡርሓን አደራጅተዉ ለሱዳን መፍትሔ ያመጣል ብለዉ ቢያቀርቡትም ከዉስጥም ከዉጭም እዉቅና አለማግኘቱ ደግሞ ሌላ ፈተና ነዉ።
እዉቅና ባለማግኘቱ ድጋፍም የለዉም ድጋፍ ከሌለዉ ደግሞ አንድ እርምጃ ወደፊት መሔድ የማይችል የትም የማይደርስ ተቋም ወይም አደረጃጀት እንዲሆን ያደርገዋል።
እነዚህ አዲስ ተመራጮች ስራቸዉን ለመከወን ባጀት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም፣ ደመወዝ ለመክፈል፣ እና ሌሎችንም ለማከናወን ባጀት የግድና የግድ ነዉ ግን ከየት ሊመጣ ይችላል? ሲል ጀማል ሮስቶም ይጠይቃል።
እነዚህን ለማሟላት ደግሞ የህዝብ መዋጮን ተማምነዉ ከሆነ በፍፁም የማይታሰብ ነዉ ያሉት ጀማል ሮስቶም የሱዳን ህዝብ አሁን ባለበት ተጨባጭ ሁኔታ ራሱን ድጎማ እና የሚያስፈለገው ህዝብ እንጅ ከእጁ እና ከኑሮዉ ያለፈ ነገር የሌለዉ የተዳከመ ህዝብ ሆኗል ይለናል ጀማል ሮስቶም።
በአፍሪካ ዓለም አቀፍ ዩንቨርስቲ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶር ዓብዱናስር በበኩላቸዉ የወታደራዊዉ ክንፍና የሉዓላዊዉ ምክር ቤት የባላደራ መንግስት መስርቻለሁ ሲል ይፋ ያደረገዉ ነገር ለፖለቲካ ፓርቲዎች ያለዉን ንቀት ግልፅ አድርጎ አሳይቶናል ይላሉ።
እንደ እኔ እይታ ከሆነ ይላሉ ዶር ዓብዱናስር እንደ እኔ እይታ ከሆነ ይኸ የባላደራ የሚባል አደረጃጀት አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ የማይችል ነዉ የህዝባዊ አመፁ መቀጠል ፣ ድጋፍ አለማግኘት፣ እዉቅና አለማግኘት፣ የመንገዶች መዘጋት፣ የባጀት አለመኖር፣ የወታደሩ ተፅእኖ እና ሌሎችም ተደማምረዉ የረባ ስራም እንዳይሰራ ያደርጉታል ይላሉ።
ወታደራዊዉ መንግስት ከአሜሪካ የልዑካን ቡድን ጋር ሆነዉ የሰጡት መግለጫ አሜሪካ ለዚህ ለባላደራዉ መንግስት ያላቸዉን ድጋፍ ያሳየ ነዉ ያሉት ደግሞ ሌላኛዉ የፖለቲካ ተንታኝ ዶር አልፋቲህ ዑስማን ናቸዉ።
በእርግጥ ይኸ የባላደራ መንግስት በርካታ ፈተናዎች አሉበት በዉጭ በኩል የአፍሪካ ህብረትን፣ የአዉሮፓ ህብረትን፣ የአሜሪካ መንግስትን፣ የእንግሊዝን፣ የዓለም ባንክን እና የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትን ድጋፍ ማግኘት የግድ ይለዋል።
በሐገር ዉስጥ ደግሞ እንደ ሰደድ እሳት እየተዛመተ ያለዉን የተቃዉሞ ንቅናቄ ለማስቆም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስምምነት እንዲኖር ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ይህ ደግሞ አሁን ሱዳን ዉስጥ ባለዉ ተጨባጭ ሁኔታ የህልም እንጀራ ነዉ ይላሉ ዶር አልፋቲህ ዑስማን።
አሁን የተደራጀዉ መንግስት በተንቀሳቃሽ አሸዋ ላይ የሚሄድ መኪና ማለት ነዉ በዛ ላይ ደግሞ እዉቅና የተነፈገዉ መንግስት ነዉ ስለዚህ ከንቱድ ድካም ነዉ ያሉት ደግሞ በልማትና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ምሁር የሆኑት ኡስታዝ ሙሐመድ ዑመር ፈይሰል ናቸዉ።
አልየዉም አልታሊ
ጃንዋሪ 25/2022