የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ከተፈጥሮ የሚያገኛቸው በርካታ ችሮታዎች አሉት፡፡ ይህን የተፈጥሮ ገጸ በረከት በምድር ሲኖር ያለገደብ ይጠቀምበት ዘንድ መብት ተሰጥቶታል፡፡
መብቶቹ በአገረ መንግሥት አስተዳደር ሂደት እንዳይጣሱ አገራት በሚያዘጋጁት ሕገ መንግሥትም ይሁን በመመሪያዎች ላይ ሕግ ጠቅሰው አንቀፅ ቆጥረው ለመብቶቹ ጥበቃም ይደረጉለታል፡፡
ምንም እንኳን ዓለም ተስማምቶ በይሁንታ ያጸደቋቸው የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ቢኖሩም በተለያየ መንገድ መብቶቹ ሲጣሱ ይታያል፡፡
በተለይም ግጭት እና አለመረጋጋት በሚታይባቸው አገራት እና አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በስፋት ይታያሉ፡፡
ዓመት ከመንፈቅ ሊሞላው ከመዳፍ ጣት ያነሰ ወራት የቀረው በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከሰብዓዊ መብት ጥሰት አልፎ ፤ ለበርካቶች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡
በርካታ ሕፃናት ለህልፈት እና ለአካል ጉዳት፤ ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት ተጋልጠዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እንዲነሳባት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከአዋሽ ሬድዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የመብቶች እና ዴሞክራሲ እድገት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ኃይሉ መንግሥት አንደ በላይ ኃላፊነቱ የሰብዓዊ መብት የሚከበርባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት አንዳለበት አንስተው፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የታጣቂ ኃይሎች እንቅስቃሴ የበርካታ ዜጎችን ሰብአዊ መብት እየተጣሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዓመት በፊት የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ በኢትዮጵያ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አንዳለ የሚያነሱት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም በጦርነት ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የመብት ተሟጋቾች እና የመገናኛ ብዙኃን ለመመርመር ፍላጎት ቢያሳድሩም አስቻይ ሁኔታዎች አለመኖራቸውን አንስተዋል፡፡
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ያለው ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ የመገናኛ ብዙኃን እና የመብት ተሟጋች ግለሰቦች ላይ ጫና እየደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲታረሙ እና አጥፊዎችም በሕግ የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙ የሲቪክ ማኅበራት ሚና ትልቅ እንደሆነ የሚያነሱት አቶ በፍቃዱ ባለፈው ስርዓት የሲቪክ ማኅበራት እንዲዳከሙ ሲሠራ መቆየቱ ለሰብዓዊ መብት መከበር የሚታገሉ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት አንዳይኖሩ አድርጓል ይላሉ፡፡
ያሉትም የሲቪክ ማኅበራት ጦርነት ቀጠናዎች ላይ ገብተው ምርመራ የሚያደርጉበት ምቹ ምህዳር አለመኖሩን አቶ በፍቃዱ ያነሳሉ፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዜጎች ላይ ደርሷል ያሉት አቶ ያሬድ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በግለሰብ እና በመንግሥት ተቋማት ከሚደረገው እርብርብ ጎን ለጎን በጦርነቱ አካባቢ ያለውን ማኅበረሰብ ስነ-ልቦና ለመጠገን እርብርብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡አንቅስቃሴው በቂ ባይሆንም የተወሰኑ ድርጅቶች ወደ ሥራ መግባታቸው ጨምረው ጠቁመዋል፡፡
ከአዋሽ ሬድዮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁለት ገፅ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ከሦሰት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የመጣውን የመንግሥት ስርዓት ለውጥ ተከትሎ ለኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ እንቅፋት የነበሩ መመሪያዎች ትርጉም ባለው መልኩ መሻሻለቸውን ኮሚሽነሩ ያነሳሉ፡፡
ነገር ግን ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየው ግጭት እና አለመግባባት አገሪቱን ወደ ሰብዓዊ መብት ቀውስ እንዳስገባት ዶ/ር ዳንኤል ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት አሳሪ የነበሩ ሕጎችን እና መመሪያዎችን ከማሻሻል ባለፈ እየወሰዳቸው ያሉ ያልተገቡ እርምጃዎች ቆም ብሎ ማሰብ እንዳለበት ያነሱት አቶ ዳንኤል ዜጎች ላይ የሚደሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል በቁርጠኝነት መሥራት አንደሚገባውም ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
በጦርነት ሳቢያ የሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል የመብት ተሟጋች ድርጅቶች እና መንግሥት በቅንጅት መሥራታቸው ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው፡፡ ተፈጥሯዊ ለሆነው የሰብዓዊ መብት መከበር ሁሉም ዜጋ የሃይማኖት አባቶች እና መንግሥት በቅንጅት እና በትብብር መሥራት ይገባዋል፡፡
የዘገበው፡- ይስሃቅ አበበ