በኢትዮጵያ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከገለልተኝነት የራቀ እንዳልሆነ በተለያዩ ጊዜያት ተመልክተናል ።
ከሙያ ስነ-ምግባር ወጣ በማለት በየጊዜው ሀገርን ከመሩ ድርጅቶች ጋር ስማቸው ሲያያዝ ማየት የተለመደ ነው ።
ይህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ወደ አንድ ፅንፍ እንዲያዘነብሉ ሲያደርጋቸው ቆይቷል ።
ባለፋት አስር አመታት የግል የመገናኛ ብዙኃን መቋቋም የተወሰነ ሚዛን የደፋ የሚመስል ስራዎች መታየት ቢጀምሩም የተጠበቀውን ያክል ግን ፍሬ ሲያሩ አልታየም።
ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሚገለፀው የመንግስት ጣልቃ ገብነት እና ሙያን በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች መለወጥ እንደሆነ በዘርፋ ተሰማርተው ዘመናትን ያስቆጠሩ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል ።
በቅርቡ በሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ላይም የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከወትሮው በተሻለ ጎላ ብሎ ይታያል ተብሎ ይጠበቃል ።
ይሁን እንጅ የሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ሀገርን ወደ አንድ የተሻለ እርምጃ ይወስዳታል ተብሎ የሚጠበቅ እንደ መሆኑ መጠን በዘርፋ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ባለሙያዎች ሀገራዊ ምክክሩን በምን አይነት ሁኔታ መዘገብ አለባቸው? ምንስ ሊያሟሉ ይገባል? ሲል አዋሽ ሬድዮ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አነጋግሯል።
ሀገራዊ ምክክሩ ሳይጀመር አስቀድሞ የመገናኛ ብዙኃን ለሁሉም ማህበረሰብ ስለ ሀገራዊ ምክክሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ የኢትዮ ኤፍኤም ስራስኪያጅ አቶ ወሰን የለህ ጥላሁን ገልፀዋል ።
ውይይቱም ከተጀመረ በኋላ ከተለያዩ ተወያዮች የሚነሱ ኃሳቦች ስለሚኖሩ ፅንፍ የረገጡ ኃሳቦች አፈትልከው እንዳይወጡ የተለየ ጥንቃቄ በዘገባ ወቅት ሊያደርጉ ይገባል በማለት አቶ ወሰን የለህ ጨምረው ተናግረዋል።
የመገናኛ ብዙኃን በቅድሚያ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉትን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በምክክሩ ወቅት ግን ከየትኛዉም የምክክሩ ተሳታፊ ጎን ሳይሆኑ ሀገርን አንድ የሚያደርጉ ኃሳቦችን ለማህበረሰቡ ተዳራሽ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርገዉ ሊሰሩ ይገባል ፡፡
የተለያዩ ኃሳቦችም የሚንፀባረቁበት ይሆናል ተብሎ ስለ ሚገመት የሚነሱ ኃሳቦችን በደንብ ማጣራትም ይገባቸዋል ሲሉ የፖለቲካል ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ዶክተር ደጉ አስረስ ተናግረዋል ፡፡
በኢትዮጵያ መንግስታት ሲቀያየሩ የመገናኛ ብዙኃን ግን እንዳሉ በመሆናቸው ያለውን ነባራዊ የፖለቲካ እውነታ ስለ ሚያውቁት ለምክክሩ ትልቅ ግብአት መሆን ስለሚችሉ በምክክሩ መድረክ በቅድሚያ እራሳቸውን ችለው ሊወከሉ ይገባል የሚሉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ጥበቡ በለጠ ናቸው።
አቶ ጥበቡ አክለውም በምክክሩ ወቅት የመገናኛ ብዙኃን ዘገባቸውን ሀገራዊ አንድነትን ማምጣት በሚችሉ መልኩ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መዘገብ አለባቸው ብለዋል ።
ነገርግን ከምክክሩም በፊትም ሆነ በኋላ በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት መስፈን የሚችልበትን መንገድ የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳቸው አድርገው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅት የህዝብ ዐይን እና ጆሮ መሆን ሲገባቸዉ ወደ አንድ ወጎን የሚያዘነብሉ መገናኛ ብዙኃን አሁን ላይ እራሳቸዉን ችለዉ ሊቆሙ እና በኢትዮጵያ የህግ የበላይነት እንዲሰፍን በተቋቋሙበት የሙያ ስነ ምግባር ስራቸዉን ሊሰሩ ይገባል ተብሏል ፡፡
የዘገበው፡- ዮሐንስ አበበ