አፍሪካ አህጉር ለምለም ነገር ግን ደሀ እናት ናት፡፡ ክንፍ እያላት የማትበር ፔንግዮን ወፍ የሚሏትም አሉ፡፡
ለድህነቷ ምክንያቱ የለምለምነቷ የሚፈጥረው የውስጥና የውጭ ጠላት መሆኑን መስማት ደግሞ ለነዋሪዎቿ ያማል፡፡
አፍሪካ ከድህነቷ መላቀቅ ያልቻለችው ተቆርቋሪ ልጆችና መሪዎችን አለማፍራቷ መሆኑን መስማት የተለመደ ሲሆን የነቁ መሪዎች ብቅ ሲሉ በውጭ ሴራና በውስጥ አመፃ ብዙም ሳይቆዩ ሲጠፉ መታየቱ ደግሞ ሌላ ህመም ነው፡፡
እንግዲህ የውስጥ አምባገነኖችና የግላቸውን ፍላጎት ብቻ የሚያስቀድሙ የጎበዝ አለቆችን መሻትና የነጮች ዘመንን የተሻገረ ወረራና ሴራ አፍሪካን እያላት ደሀ አድርጓታል፡፡
ህዝቦቿ በጦርነት፣ በድህነት፣ በርሀብና በስደት አረር እየተለበለቡ ቀጥለዋል፡፡
በአሁኑ ዘመን እንኳን በየዓመቱ ከአንድ እና ከሁለት በላይ መፈንቅለ መንግሥቶች በአህጉረ አፍሪካ እየተካሄዱ ህዝቦች ለስቃይና እንግልት መዳረጋቸው የተለመደ ባህል ነው፡፡
በያዝነው አመት ብቻ በአፍሪካ አምስት መፈንቅለ መንግሥቶች መካሄዳቸውን ልብ ይለዋል፡፡
መፈንቅለ መንግሥቱ ባልተካሄደባቸው ሌሎች ሀገራትም ጦርነትና ርሀቡ አለ፤ ሽብርተኝነትና ዝርፊያውም ቦታውን አለቀቀቀም፤ ሙሰኝነትና አምባገነንነቱ የሰዎችን ተፈጥሯዊ መብት እንደነፈገ በሌላ ጥግ ቀጥሏል፤ እዳና ብድሩም ባለበት አለ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ድርቅና ጠኔው፣ ቁርና እርዛቱ የሚለበልባቸው የለምለም ራቁት ሀገራት በብዛት የሚታይባት አህጉር ናት አፍሪካ፡፡
የድህረ ቅኝ አገዛዝ አዝማሚያውም ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ደቡብ የአፍሪካ አሀገራት ውሰጥ ውስጡን እንደ እሾህ እየተተከለና እንደ ባሩድ ጭስ እያጠናት ይገኛል፡፡
መዘርዘሩ ካልሰለቸ የአፍሪካ ጉድ ብዙ ነው፡፡
ታዲያ ሁኔታውን በቋሚነት ለመለወጥ ታስቦ የታቀደ ዘዴ እንዳለ ይታወቃል፡፡ አጀንዳ 2063 ይሰኛል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ያስቀመጠው ባለ 7 ግብ እቅዱ ሰላምና ብልፅግናን፣ አንድነትና ትስስርን ለማስፈን የተቀመጠ ነው፡፡
እቅዱ ሁሉም የአፍሪካ ሰው በልቶ እንዲያድር እና ከድህነት እንዲላቀቅ ከማለሙ በተጨማሪ በአህጉሪቱ ምንም ዓይነት የጠመንጃ ድምፅ እንዳይሰማም አቅዷል፡፡
ይህ እቅድ ለዚህች አመለኛ አህጉር በጣም የተራቀቀና የራቀ የሚመስል ነው፡፡ በብርቱ ከተሰራበት ግን የማይደረስበት ተምኔት አለመሆኑን ዘርፉን የሚያጠኑ ሊኅቂን ይናገራሉ፡፡
ጥያቄው ግን ሀገራቱ በሚጠበቀው ልክ እየሰሩ ነው ወይ? የሚለው ይሆናል፡፡
ሠላሳ ዓመት ለቀረው ለዚህ ትልቅ ግብ ሩጫው ከዚያ በሚያደርስ ፍጥነት ተጀምሯል ወይ? የሚል ጥያቄም ማንሳት ይቻላል፡፡
የዛሬው የአዋሽ ትኩረታችን ተግዳሮቶችና መልካም እድሎችን እንዴት ማየት ይቻላል ሲል የዓለምዓቀፍ ፖለቲካ አጥኚ ሙሁራንን አነጋግሯል፡፡
ወርቁ ያዕቆብ (ዶ/ር) የእስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዓለምአቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ እቅዶች ጥሩ ናቸው ነገር ግን እቅዶቹ በሚሳኩበት ደረጃ ሲሰራ እያየን አይደለም የሚለውን ተናግረው ርብርቦች እንደሚያስፈልጉ ይጠቁማሉ፡፡
ዶ/ር ወርቁ አክለውም ሰሞኑን የተካሄደው 35ተኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ እንኳን ተሰበሰቡ ሲባል ከመስማታችን ውጭ ምን እንዳቀዱ፣ በምን በምን ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ላይ እንደደረሱ ሲገልፁ አላየንም ይላሉ፡፡
መሰባሰቡ ብቻ ለውጥ እንደማያመጣ የሚናገሩት ሙሁሩ አጀንዳ 2063 እንዲሳካ ከተፈለገ ከፍተኛ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል፡፡
ሌላው የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ አጥኚ ሐብታሙ ገ/መድህን በአፍሪካ አህጉር ያለው መፈንቅለ መንግሥት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ የተፋዘዘ ኢኮኖሚያዊ እድገት፣ የህብረቱ ውሣኔዎች አስፈፃሚ ማጣትና የውጮች ጣልቃ ገብነት ካልተቀረፈ አጀንዳ 2063ትን ማሳካት ይከብዳል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ አጀንዳ 2063ትን የሀገር ውስጥ እቅዷ አካል አድርጋ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሐብታሙ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ግብን እቅድ ከማድረጋቸው ውጭ የራሳቸው አህጉር እቅድ በውስጣቸው የልማት ፖሊሲ ሲያካትቱት አይስተዋልም ይህ ደግሞ አንዱ የታለመውን እንዳይሳካ የሚያደርገው ነው፡፡
ስለሆነም ሀገራት የውስጣቸውን እድገት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት አለባቸው፤ አጠቃላይ ድምሩም ከዚያ የሚወጣ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርስቲ የዓለምአቀፍ ግንኙነትና ፖለቲካል ሣይንስ መምህሩ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) የታለመው አጀንዳ 2063 እንዲሳካ ሀገራት የውስጥ ሰላማቸውን ማስፈንና የነጮችን ጣልቃ ገብነት በፅኑ መከላከልና ማስቆም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
አጀንዳ 2063 ተሳክቶ አፍሪካ እንደታሰበው የበለፀገችና የጥይት ድምፅ የማይሰማባት እንድትሆን የውስጥ ሰላምና እድገትን ማፋጠን ከዚያ አልፎም የነጮችን ጣልቃ ገብነት መቃወም ያስፈልጋል የሚለው የሁሉም ሙሁራን ኃሣብ ነው፡፡
በያለው አዛናው