አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠታቸዉ በዜጎች ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል…።
የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግርማ በቀለ
በአሳለፍነው አንድ አመት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከሰተው ጦርነት በርካታ የሰውና የንብረት ውድመቶቸች መከሰታቸዉ የሚታወስ ነው፡፡
በተደረገው ጦርነትም ይበልጡን ተጎጂ የሚሆኑት ሴቶችና ህፃናት እንደሆኑ እየወጡ የሚገኙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡
የስነ-ልቦና ጉዳቶች ጦርነቱ ቢያበቃም እንኳ ከአካል ጉዳት በዘለለ የከፋ ቀውስ በህፃናት ላይ ጎልቶ ሊታይ እንደሚችል በአለም ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡
በመሆኑም እነዚህን ጉዳቶች ለመቀነስ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያሻ በተደጋጋሚ እየተነገረ ቢሆንም አሁንም ግን የጦርነቱ መዳረሻ እስከምን ድረስ መሆኑ አለመታወቁ ችግሮቹ እንደሚቀጥሉ ማሳያ ነው፡፡
በተለይ ጦርነቱ በተከፈተባቸዉ የአማራ እና የአፋር ክልሎች ላይ የሕውሓት ሽብርተኛ ቡድን አሰቃቂ ወንጀሎችን መፈፀሙ የቅርብ ወራት ትውስታ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ቡድኑ በመንግስት በደረሰበት ጥቃት ይዟቸዉ ከነበሩ ክልሎች ወቶ ቢቆይም ባሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ግን ዳግም ወደጥቃት መመለሱን የአፋር ክልል በመግለጫዉ አመላክቷል፡፡
ክልሉ እንደ ገለፀዉም የሕውሓት ሽብርተኛ ቡድን አሁን ላይ ህፃናትና ሴቶችን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየፈፀመ እንደሆነ አስታዉቋል፡፡
በመሆኑም መንግስት ጉዳዩን እንዴት መመልከት አለበት? ምንስ ሊያደርግ ይገባል? ሲል አዋሽ ሬድዮ የፖለቲካ ፓርተዎችን አናግሯል፡፡
መንግስት የሚያስተዳድረዉን ህዝብ ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት በመሆኑም የሽብር ቡድኑ በድጋሚ በአፋር እና አማራ ክልሎች ላይ እያደረሰ የሚገኘዉን ጥፋት በአፋጣን ምላሽ የሚሰጥበትን ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል ሲሉ የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር ስይፈስላሴ አያሌዉ ተናግረዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ተመልሶ ጥቃት መክፈቱን በተደጋጋሚ የክልሉ መንግስት እያስታወቀ ቢሆንም የሚመለከታቸዉ አካላት አፋጣኝ ምላሽ ባለመስጠታቸዉ በዜጎች ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል ያሉት ደግሞ የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግርማ በቀለ ናቸው፡፡
ቡድኑ ታሪክም እንደ ሚያስረዳዉ በደዚህ አይነት አጋጣሚዎች እረፍት ሲያገኝ መልሶ ለማጥቃት እራሱን እንደ ሚያደራጅ ይታወቃል፡፡
አለፍ ሲልም እወክለዋለሁ የሚለዉን ህዝብ በማስገደድ ወደ ጦር ግንባር ሊማግደዉ ስለሚችል አላስፈላጊ መስዋትነት ከመከፈሉ አስቀድሞ አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል በማለት ዶክተር ሰይፈስላሴ አያሌዉ ተናግረዋል፡፡
ችግሩ በድጋሚ የተከሰተው በመንግስት የሚወሰኑ ዉሳኔዎች ግልፅነት የጎደላቸዉ በመሆናቸዉ እንደዚህ አይነት መሰል ጥቃቶች በድጋሚ ሊከሰቱ ችለዋል፡፡
ችግሮች ከተከሰቱም በኃላ መንግስት የሽብር ቡድኑ በህፃናት እና በሴቶች ላይ እያደረሰ የሚገኘውን ጉዳት ለአለም አቀፋ ማህበረሰብ እዉነታውን መንግስት ሊያስረዳ ይገባል ሲሉ አቶ ግርማ በቀለ ጨምረዉ ገልፀዋል፡፡
የሕውሓት ሽብርተኛ ቡድን በድጋሚ እያደረሰ የሚገኘዉ ጥቃት በአፋጣኝ መመለስ ካልተቻለ ቡድኑ አድማሱን የሚያሰፋባቸዉ አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ስለሚችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ከወዲሁ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ፓርቲዎቹ ኃሳባቸዉን አጋርተዋል፡፡
በዮሐንስ አበበ