Connect with us

ዲፕሎማሲ

አዲሱ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስና የሓያላን ሐገራት ፉክክር፡ ክፍል 4

Published

on

featured
Photo: Wikipedia

ሓያላን ሐገራት የአፍሪካ ቀንድ ሐገራትን ለመከፋፈል እና በእጅ አዙር ዘመናዊ ቅኝ ግዛት ስር ለማድረግ የሚያደርጉት እሩጫ አሁንም እንደቀጠለ ነዉ ከራሽያ ኦክራንያ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ ደግሞ የምዕራባዊያን ዓላማ ከመቸዉም ጊዜ በበለጠ ግልፅ እየሆነ መጥቷል መላዉ አፍሪካዊያን እና ዓረቦች ከኦክራንያ ጎን እንዲሰለፉ ጠየቀዋል የተለያዩ ማግባቢያዎችንና ማባበያዎችንም ለመጠቀም ሲሞክሩ እየተስተዋሉ ነዉ።

ለዚህ ማሰረጃ ብዙም ርቀን ሳንሔድ የሱዳንን እና የግብፅን ሁኔታ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል ።

ሙሐመድ ሓምዳን ደቅሎ ወይም ሓሚደቲ በሚል ቅፅል ስማቸዉ የማታወቁት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት በባለፉት ሳምንታት ወደ ራሽያ ተጉዘዉ የነበረ ጊዜ የሱዳን መንግስት ከራሽያ ጎን እንደሚሰለፍ በይፋ ሞስኮ ሆነዉ ቢናገሩም ይህን የሱዳን አቋም ለማስቀየር ግብፅ መራሹ የዐረብ ሊግ በአንድ ወገን በእንግሊዝ የሚመራዉ የምዕራባዊያን እና የአሜሪካ ቡድን በሌላ ወገን ሆነዉ ሱዳንን እያስጨነቁት ነዉ።

ከዚሁ ከራሽያ ኦክራንያ ጦርነት ሳንወጣ ሳዑዲ ዓረቢያ የገልፍ ዐረብ ሐገራትን ግብፅ ደግሞ ከሌሎች የዐረብ ሐገራት በተጨማሪ የሰሜን አፍሪካ የዐረብ ሐገራትን እንዲያሳምኑ ግዴታ ተጥሎባቸዉ የማሳመን ስራቸዉን በይፋ ጀምረዋል የግብፁ ፕሬዚደንት ዓብዱልፈታህ አለሲሲ የሰሞኑ የሳዑዲ ዐረቢያ ጉብኝታቸዉ ሚስጥርም ይኸዉ ነዉ።

ግብፅ ተሳክቶላት የዐረብ ሊግ አባል ሐገራት ከኦክራንያ ጎን እንዲሰለፉ ካደረገች እንደ ትልቅ የህልዉና ስጋት የምትቆጥረዉን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጄክትን ጨምሮ ሌሎች በአፍሪካ ቀንድ የራሷን ጥቅምና መብት ሊያስጠብቁለት በሚችሉ ነገሮች ላይ ምዕራባዊያን ከጎኗ እንዲሰለፉ ልታስገድዳቸዉ ትችላለች የሚሉ የምሁራን አስተያየቶች እየተበራከቱ ነዉ።

በባለፈዉ ሳምንት ማለትም በክፍል 3 ዝግጅታችን የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስና ሳዑዲ ዓረቢያ በአፍሪካ ቀንድ ሐገራት ያሉ ወደቦችን በቁጥጥራቸዉ ስር ለማድረግ የሚያደርጓቸዉን ሩጫዎችና ስኬቶቻቸዉን ተመልክተናል።

በዛሬዉ ዝግጅታችን ደግሞ የኢመሬትስና የሳዑዲ ዓረቢያ ተቀናቃኝ የሆኑት ቱርክና ኳታር በሱማሊያ በሱዳን እና በኤርትራ ምን ለማድረግ አቅደዋል? የሱማሊዋን ሖቢዮ ወደብ ለማልማት የታሰበዉስ ለምንድነዉ? ቱርክ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታደርጋቸዉ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴዎች ለቀጣናዉ ህዝቦች ያለዉ አዎንታዊና አሉታዊ ጎንስ ምንድነዉ? ኳታር ከቱርክ ጋር ተጣምራ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታሳያቸዉን የተቀናቃኝ ስሜትስ እነ ሳዑዲ ዓረቢያ እንዴት እያዩት ነዉ የሚሉትን ቁልፍ ነገሮች እናነሳለን።

እስከ ፕሮግራማችን ፍፃሜ አብራችሁን ትሆኑ ዘንድ ከወዲሁ እጋብዛለሁ ።

ምንም እንኳን ኳታርም ሆነች ሳዑዲ ዓረቢያ ኢመሬትስም ኩዌይት ሁሉም የገልፍ ዐረብ ሐገር አባል ቢሆኑም ኳታር የምታራምደዉ አስተሳሰብ ከሌሎች የገልፍ ዐረብ ሐገራት የተለዬ በመሆኑ የገልፍ ዓረብ ሐገራት ኳታርን ለማግለል እስከ ማዕቀብ የደረሰ ጫና ሲያደርጉባት እንደነበረ የምናስታዉሰዉ ሐቅ ቢሆንም ኳታር ግን በዐለማችን ከእነ ቢቢሲ እና ሲ ኤን ኤን ተርታ የሚመደበዉን ግዙፍ ሚዲያዋን ተጠቅማ የእነሱን የጥላቻ እና የማግለል ዘመቻ ለመመከት እና ለመቋቋም ችላለች።

ከዛም ባለፈ ኳታር ከሱማሊያ መንግስት ጋር በ 2018 አድርጋዉ በነበረ ስምምነት የሱማሊያን ወደቦች አልምታ የመጠቀም እድል አግኝታ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።

ታዲያ በዚህ ስምምነት መሰረት ከሱማሊያ ዋና ከተማ ከመቋዲሹ በሰሜን ምስራቅ በኩል 483 ኪሜ ርቀት ላይ የምትገኘዋን የሆቢዮ ወደብ አልምታ ለመጠቀም በተግባር እንቅስቃሴዋን ጀመረች።

ከኳታር ጎን ሁሌም ቢሆን የማትጠፋዉ ቱርክም የኳታርን እግር እየተከተለች ሁለቱ ሐገራት እየተናበቡና እየተቀናጁ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር አካባቢ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጠናክረዉ ቀጠሉበት።

በ 2017 በገልፍ ዓረብ ሐገራት አካባቢ ተፈጥሮ የነበረዉን ቀዉስ ተንተርሳ ቱርክም የራሷን ጥቅም የማስከበርና እጅግ ስትራቴጂክ ስለመሆኑ በስፋት በሚነገርለት ቀይ ባህር አካባቢ በስፋት መንቀሳቀሱን ተያያዘችዉ።

የቱርክን በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር  አካባቢ መታዬት ያልወደዱት ሳዑዲ ዐረቢያና ግብፅ ደም ፍላታቸዉ እጨመረ ጅማታቸዉ ሲግተረተር ግንባራቸዉ ላይ በግልፅ ይታይ ነበር እናም ግብፅ መራሹ የዐረብ ሊግ በጠራቸዉ ስብሰባዎች ሁሉ ቢገጥምም ባይገጥምም የቱርክ ስም ሳይነሳ ቀርቶ አያዉቅም።

በያዝነዉ ሳምንት እንኳን የዐረብ ሊግ 157 ኛዉን የሚኒስትሮች ጉባኤ ሲያካሒዱ የቱርክ ጣልቃ ገብነት እንቅልፍ ነስቶናል ሲሉ ተደምጠዋል። እዚህ ላይ አንድ ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነዉ የቱርክ ነገር ዓረቦችን ይህን ያህል ያስጨነቃቸዉ ለምንድነዉ? ዐረቦች በእስራኤል ምክንያት ህይወታቸዉ የተመሰቃቀለባቸዉን ፍልስጤሞች ጉዳይ ቸላ ብለዉ  የቱርክ ጉዳይ እንቅልፍ ነስቶናል ብለዉ መጨነቃቸዉ የጤና ማጣት ወይም እብደት ካላልነዉ በስተቀር ምን ልንለዉ እንችላለን?

ይዉጣላችሁ በሚል መንፈስ ይመስላል ቱርክም በቀይ ባህር አካባቢ ያላትን እንቅስቃሴ አጠናክራ ቀጠለችበት እናም አነሆ ቱርክ በ 2018 እነ አል ቡርሓን መፈንቅለ መንግስት አድርገዉባቸዉ አሁን ከርቸሌ ከገቡት ከዑመር ሐሰን አል በሽር ጋር በፈረመችዉ ስምምነት 20 ኬሜ እርዝመት ያለዉንና የብዙዎችን ቀልብ የገዛዉን ቀድሞዉንም በኦቶማን ኢምፓየር ስር የነበረዉን የሰዋኪን ወደብ አልምታ ለመጠቀም ስራዋን በይፋ ጀመረችዉ።

በዚህ የቱርክ እንቅስቃሴ ያዙኝ ልቀቁኝ ያለችዉ ግብፅ ቀድሞዉንም የአል በሽር መንግስት የሙስሊም ወንድማማቾችን ወይም በእንግሊዝኛዉ አጠራር Muslim brotherhood ን እያሰለጠነ ይልክብኛል ይህ አልበቃዉ ብሎት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ተወዳጅቶ ቁም ስቅሌን እያሳየኝ አሳሬን እያበላኝ ስለሆነ መዉደቅ አለበት ብላ በመወሰኗ የአል በሽርን ተቃዋሚዎች በማሰልጠንና በመደገፍ የሱዳን መንግስት ለረጅም ዓመት ሰላሙን እንዲያጣ አደረገች ግብፅ።

እናም አነሆ በ 2019 በአል በሽር ላይ መፈንቅለ መንግስት ተካሒዶ አሳቸዉም አስር ቤት በመግባታቸዉ ከቱርክ ጋር ተፈርመዉ የነበሩት ስምምነቶችም ዉሓ በልቷቸዉ ባሉበት ቆመዉ ይገኛሉ።

ቱርክ በ 650 ሚሊዮን ዶላር አልምታ ለ 99 ዓመት ልትጠቀምበት የነበረዉ የሰዋኪን ወደብንና አካባቢዉን የማልማት ፕሮጄክት የመጨናገፍን ነገር እሰይ እንኳን ተጨናገፈ ነዉ የሚባለዉ? ወይስ በዚህ ፕሮጄክት መደናቀፍ ሱዳን በርካታ ጥቅሞችን አጣ ነዉ የሚባለዉ? መልሱን ለእናንተ እተወዋለሁ።

የሱዳኗ ሰዋኪን ወደብ ከፖርትሱዳን 40 ኪሜ ብቻ የምትርቅ ዘመናዊና ቱርክ ቀመስ ወደብ ጉዳይ ዑመር አል በሽር የገጠማቸዉ ነገር ባይገጥማቸዉ ኖሮ እህኔ ዘመናዊ ወደብ ሆና ፣ የቱርክ ወታደሮችም በአካባቢዉ ሰፍረዉ፣ የቱርክ መንግስትም ለሱዳን ወታደሮች ሽብርተኝነትን የመከላከል ወታደራዊ ጥበብ አስተምሯቸዉ፣ የሱዳን ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተጧጡፈዉ እንመለከት ነበር።

እነ ሳዑዲ እና ኢመሬትስ በቀይ ባህርና አፍሪካ ቀንድ አካባቢ የወጠኗቸዉ ፕሮጄክቶች ተሳክተዉ በአንፃሩ ደግሞ የእነ ኳታርና ቱርክ ዉጥኖች ግን ገና ከጅምሩ ሲኮላሹና ፈተና ሲበዛባቸዉ ስንመለከት ከእነ ሳዑዲ ጀርባ ማን እንዳለ እና ከእነ ኳታር ጀርባ ደግሞ የእነ ማን ድብቅ ዓላማና ፍላጎት እንዳለ በቀላሉ ማወቅ እንችላለን እናም ለዚህ ነዉ የቀይ ባህር ቀጣና በበርካታ ሓያላን ሐገራት እይታ ስር ወድቋል የምንለዉ።

ቱርኮች በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰንቀዉ የመጡት ህልምና ትልም በዚህ አያቆምም ሓሳባቸዉ የቆየ መሆኑን የምንረዳዉ በ 2014 ለመቋዲሹ ቅርብ የሆነ አካባቢን በሓይል ይዘዉ ሁለት ኪሜ ስፋት ያለዉን አካባቢ ተቆጣጥረዉ የወታደራዊ ስልጠና መስጫ ማዕከል ማድረጋቸዉና እግረ መንገዳቸዉንም እንደነ Favori LLC የተሰኙ የቱርክ ካምፓኒዎች የመጠበቅ ስራ ጀመሩ ይህ የሆነዉ አልበርቅ የተሰኘዉ የቱርክ ልዩ ሓይል የመቋዲሹን ወደብ ማሰራት ከጀመረ በኋላ ነዉ።

ምንም እንኳን የመቋዲሹን ወደብ የመጠቀም ሓሳብ የቱርክ ፍላጎት ብቻ ባይሆንም ነገር ግን ይህን ወደብ ለመጠቀም እስከ 200 የሚደርሱ የቱርክ ወታደሮችም በአካባቢዉ እንዲሰፍሩ መደረጉ የተባበሩት ኢመሬትስም ሆነች ሳዑዲ ዓረቢያ ቱርክም ሆነች ኳታር ከኢኮኖሚያዊ ፍላጎታቸዉ ጎን ለጎን ሌላ ድብቅ የሆነ ወታደራዊ ተልእኮም እንዳላቸዉ ያሳየናል።

በባለፈዉ ዝግጅታችን ሳዑዲ ዓረቢያና ኢመሬትስ በቀይ ባህር አካባቢ በተለይም እዚህ ከኤርትራ ጋር የተፈራረሟቸዉ የወደብ አጠቃቀም እና በተለይ ደግሞ ከዐሰብ ወደብ እየተነሱ የመንን የሚያጠቁበት አካሔድ እንዲሁም ሳዑዲ ዐረቢያም በበኩሏ በኤርትራ ዉስጥ ወታደራዊ የጦር ሰፈር እንዳላት መረጋገጡ በራሱ እነኝህ ሐገራት በቀጣናችን ያላቸዉ ፍላጎት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ ቆም ብለን ልናስብበት የሚገባ አደገኛ እንቅስቃሴ መሆኑን ያሳየናል።

በርካታ ምሁራን እንደሚሉት ከሆነ አነዚህ የዐረብ ሐገራት የሶስተኛ ወገን ጥቅም ለማስከበር እንጅ ለራሳቸዉ ብለዉ የሚከፍሉት መስዋእትነት አይደለም ደግሞም እንቅስቃሲያቸዉ የራስን ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ቢሆን ኖሮ ቆም ብሎ የሚመለከታቸዉ አካል አይኖርም ነበር እንቅፋቶች ይበዙባቸዉ ነበር ይላሉ።

ዞሮ ዞሮ እነ ሳዑዲ እና ኢመሬትስ በአንድ ወገን ኳታር ቱርክን ይዛ በሌላ ወገን የሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች የየቅል መሆናቸዉን ግን ልብ ልንል ይገባል ስለሆነም አንዱ ወገን ለሌላዉ እንቅፋት እንጅ ደጋፊ ሊሆነዉ እንደማይችል ልንረዳ የግድ ይለናል።

ይህ እንዳለ ሆኖ ከጀርባ ሆነዉ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሓያላን ሐገራት ደግሞ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል በክፍል አንድ ዝግጅታችን ጅቡቲ የአምስት ሓያላን ሐገራት የጦር ሰፈር መገኛ መሆኗን ተመልክተን ነበር።

ዛሬም ይህን በተጨባጭ የሚያሳዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነዉ። ከዚህ በፊት ከጀርባ ሆነዉ ሲመሩት የነበረዉን እንቅስቃሴ ፊት ለፊት ለመምራት በሁለትዮሽ ስምምነት ስም የእጅ አዙር ዘመናዊ ባርነት ዉስጥ ለማስገባት ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸዉ።

ለመሆኑ በዚህ ረገድ ቻይና እና አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ የሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች እና ፉክክሮች ምን ይመስላሉ? የአነሱ ፉክክር በእኛ ላይ የሚያሳድረዉ አሉታዊ ተጽእኖስ ምንድነዉ? ከእኛስ ምን ይጠበቃል? የሚሉትንና ሌሎችን ቀጣናዊ ጉዳዮች በሚቀጥለዉ ሳምንት ዝግጅታችን የምንመለከታቸዉ ይሆናል እስከዛዉ ቸር ሰንብቱ።

ዑመር መኮንን ነኝ፡ ከአባይ ጓዳ – ሰላም!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ዲፕሎማሲ

አዲሱ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስና የሓያላን ሐገራት ፉክክር፡ ክፍል 3

Published

on

featured

በባለፈዉ ሳምንት ማለትም በክፍል ሁለት ዝግጅታችን የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ በአፍሪካ ቀንድ የምታደርጋቸዉን ኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን በስፋት የተመለከትን ሲሆን ወደቦች ወይም የባህር በሮች ያሏቸዉ ሐገራት ተጨማሪ ወደብ ለማግኘት የሚያደርጉት ሩጫ አንድምታዉ ምንድነዉ? በሚለዉ አወዛጋቢ ጥያቄ ላይ በስፋት ተነጋግረን ነበር።

በዛሬዉ ዝግጅታችንም ይህንኑ ጉዳይ በስፋት የምንነጋገርበት ሲሆን በተለይ ኢመሬትስና ሳዑዲ ዓረቢያ በቀይ ባህር አካባቢ በሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች ከጀርባቸዉ ማን አለ? ማንም ይኑር ማን ፑንት ላንድ አካባቢ እያደረጉት ያለዉ ያልተለመደ እንቅስቃሴስ ትርጉሙ ምንድነዉ? ኢመሬትስ እና ሳዑዲ ዓረቢያ በየመን ላይ እየወሰዱት ያለዉ ወታደራዊ እርምጃ ዓለማዉ ምንድነዉ? ግጭቱ በአፍሪካ ቀንድ ሐገራት ላይ የሚያሳድረዉ ሁለንተናዊ ተፅእኖስ ምንድነዉ የሚሉትንና ሌሎችን እንመለከታለን።

የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ ዑመር መኮንን ነኝ እስከ መጨረሻዉ አብራችሁን ትሆኑ ዘንድ ከወዲሁ እጋብዛለሁ።

የቀይ ባህር እና የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ እንጅ እየተፍታታ ሲመጣ አይስተዋልም በተለይ ከሰሞንኛዉ የራሽያ – ኦክራንያ ዉዝግብ ጋር ተያይዞ የአፍሪካ ቀንድ ሐገራት አቋማቸዉን ግልፅ በማድረጉ በኩል ሲቸገሩ እየታዩ በመሆኑ ቀጣናዉ ምን ያህል በተፅእኖ ስር እየወደቀ መምጣቱን ግልፅ አድርጎ ያሳየናል።

በኢኮኖሚ ራስን አለመቻል ለፖለቲካ ጥገኝነት ይዳርጋል የሚባለዉ አባባል ምን ያህል እዉነት መሆኑን የምንረዳዉ የአፍሪካ ቀንድ ሐገራት ከራሽያ – ኦክራንያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ለራሽያ ከወገኑ አሜሪካ እና ምዕራባዊያን ሊቀየሙባቸዉ ነዉ ለኦክራንያ እንዳይወግኑ ደግሞ ቀጣናዉን ከዉጭ ተፅእኖ ነፃ ለማዉጣትና የአሜሪካን ብቸኛ ሓያልነት የምትቃወመዉ እና የሓይል ሚዛኑን ታስጠብቃለች ተብላ የምትጠበቀዉ ራሽያ ሊከፋት ነዉ እናም በዚህ የተነሳ ቀጣናችን ግራ ተጋብቶት መመልከታችን የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦችን ሁለንተናዊ አንድነት እና ዉህደት ባስጠበቀ መልኩ የአፍሪካን አሐጉራዊ ጥቅም ለማስከበር የአፍሪካ መሪዎች  ከመቼዉም ጊዜ በበለጠ ተናበዉ እና አንድ ሆነዉ መስራት እንደሚጠበቅባቸዉ ያሳየናል።

ኢመሬትስ በ 2017 የፑንትላንዷን ቦሳሶን ወደብ ለመጠቀም ያስችላት ዘንድ ከሐገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ሰፊ ዉይይት ማድረጋቸዉ ኢመሬቶች የባህር በር አጥተዉ ሳይሆን በአንድ ዲንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ አንድም በሐብት ላይ ሌላ ሐብት ለመጨመር ሲሆን ሁለትም በቀጣናዉ እየተስተዋለ ያለዉን ፉክክር በቅርብ ርቀት ለመከታተልና ከአጋሮቻቸዉ ጋር ሆነዉ ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት እንዲያመቻቸዉ ነዉ።

በየመን እየተካሔደ ባለዉ ጦርነት በርካታ የገልፍ ዓረብ ሐገራት ነገሩን ከኢራን ጋር በማያያዝ ለመተባበር ስምምነት ላይ የደረሱበት ጉዳይ ቢሆንም በኢመሬትስ እና በሳዑዲ ዓረቢያ ጠንካራ ወታደራዊ ትብብር እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ግን ለብዙዎች ጥያቄዎችን ያስነሱ ተግባራት አየሆኑ ነዉ በተለይ ኢመሬትስ ደቡብ የመንን ሙሉ ለሙሉ በእርሷ ቁጥጥር ስር እንዲዉል ማድረጓ እዉን ይኸ የኢመሬትስ ፍላጎት ነዉ? ወይስ ኢመሬትስና ሳዑዲ ዓረቢያ ደፋ ቀና የሚሉት የሶስተኛ ወገን ጥቅም ለማስከበር ነዉ የሚለዉን የዶር ሐሰን መኪን ጥያቄ ደጋግመን እንድናነሳ ያስገድደናል።

ምንም እንኳን የኢመሬትስ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር አካባቢ የማደርጋቸዉ እንቅስቃሴዎች ለብሔራዊ ደህንነቴ አስጊ ናቸዉ ያልኳቸዉን ማለትም በኢራን የሚደገፉትን የሁሲዎችን እንቅስቃሴ ለመግታት እና የአልቃዒዳንም ንቅናቄ ለመቀነስና  ነገሮች ስጋት የማይሆኑበትን እርምጃ ለመዉሰድ ነዉ ይበል እንጅ  ዓላማዉ ግን በዉል አይታወቅም የሚሉ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ ነዉ እንዲያዉም ኢመሬትስ በየመን የምታደርገዉን እንቅስቃሴ ወረራ ነዉ እስከ ማለት የደረሱም አሉ።

ኢትዮጵያ ከገልፍ ዐረብ ሐገራት ጋር እጅግ የጠበቀ እና እስከ መጋመድ የደረሰ ትስስር አላት በተለይ የአረቢያን ደሴት ከምትባለዋ ከየመን ጋር ደግሞ በታሪክ የተመዘገበ ታሪካዊ ባህላዊ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቁርኝት አላት በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያን እንደ ሁለተኛ ሐገራቸዉ በመቁጠር ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን ለመኖሪያነት መርጠዉ በተለያዩ የሐገራችን ክፍሎች የሚኖሩ የመናዊያን ቁጥር ስፍር የላቸዉም።

ታዲያ ኢመሬትስና ሳዑዲ አረቢያ መራሹ የየመን ጦርነት  ለኢትዮጵያ ትልቅ ጭንቀትና የቤት ስራ ሆኖባታል የምንለዉ ከዚሁ ተነስተን ነዉ የጦርነቱ ዳራስ የት ድረስ ነዉ? ዓላማዉስ ምንድነዉ? ከኢትዮጵያስ የሚጠበቀዉ ምንድነዉ?  የሚሉት ጥያቄዎች ሁሌም ቢሆን እንደ ጎረቤት ተጋምዶና ተዋዶ ብሎም ተሳስሮ እንደኖረ ህዝብ መነሳት ያለባቸዉ ጥያቄዎች ናቸዉ።

ከዚሁ ከየመን ጦርነት ጋር በተያያዘ ጥርጣሬዎች እንዲፈጠሩብን ያደረገዉ የኢመሬትስ እንቅሰቃሴ በዚህ አላበቃም ኢመሬትስ የሱማሌ ላንድን የጅቡቲን የፑንት ላንድንና የኤርትራን ወደቦች በኪራይም ሆነ በሌላ ስምምነት የራሷ ካደረገች በኋላ የመንም ዉስጥ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች መሆኗ ነዉ።

የየመኗን ብሬም ወደብ በ 2016 ከተቆጣጠረች በኋላ ወዲያዉኑ የአዉሮፕላን መንደርደሪያና ማረፊያ መስራቷ ኢመሬትስ በየመን ዉስጥ ማሳካት የፈለገችዉን ትክክለኛ ዓላማ ለማወቅ ነገሮችን የበለጠ እያወሳሰበብን ነዉ።

ሆኖም ግን ከሳተላይት የተገኙ ምስሎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ኢመሬትስ በብሬም ወደብ ጀምራዉ የነበረዉን ግንባታ በሁሲዎች ተከታታይ እና ጠንካራ ጥቃት ምክንያት እንዳቋረጠችዉ ያሳያል።

እጅግ የሚገርመዉ ደግሞ የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ ከብሬም ወደብ ሲባረሩ የሱቁጥሪን ወደብ ለመቆጣጠር በ 2018 በታንክና በአየር የታገዘ ጥቃት ፈፅመዉ በሱቁጥሪ ወደብ ላይ የኢመሬትስን ሰንደቅ ዓላማ ማዉለብለብ መጀመራቸዉ የየመንን መንግስትና የየመንን ህዝብ ቁጣ ቀስቅሶ እንደነበረ ማስታወስ በጣም አስፈላጊ ነዉ።

ሆኖም የብሬንን ወደብ በሁሲዎች ጥቃት ሳቢያ ለቀዉ እንደወጡት ሁሉ የስቁጥሪን ወደብ ደግሞ በሳዑዲ ዓረቢያ አደራዳሪነት ለቀዉ እንዲወጡ ሆኗል።

የመን ዉስጥ እጅግ ታሪካዊና ትልቅ ከሚባሉት ከተሞች መካከል ዐደን አንዷ ናት ታዲያ በዚች ባለ ወደብ ከተማ ወደቡን ለመቆጣጠር ኢመሬቶች ከዚህ በፊት በኪራይ መልክ ከተቆጣጠሩት ከኤርትራዋ ዐሰብ ወደብ ተነስተዉ ማጥቃት ጀመሩ ከዛም በጊዜዉ ኢመሬትስ ከሌሎች አጋሮቿ ጋር ሆና የዐደንን ወደብ ለመቆጣጠር ችላለች።

የዐደን ወደብ በዓለማችን እጅግ ስትራቴጂክ ከሚባሉት መካከል አንዷ ናት ዓለም አቀፍ ንግዶች ይካሔዱባታል ከባበል መንደብም በቅርብ እርቀት የምትገኝ ስለሆነች እና ከዚህ በፊትም የእንግሊዝ ወታደራዊ እና የንግድ ማዕከል ስለነበረች ወሳኝነቷ አጠያያቂ አይደለም።

የተባባሩት ዓረብ ኢመሬትስ በቀይ ባህር አካባቢ የምታደርገዉ ወታደራዊና ኢኮኖማያዊ እንቅስቃሴ ከኢመሬትስ አቅም በላይ ነዉ ስለሆነም በርካታ ምሁራን እንደሚናገሩት ከሆነ ከኢመሬትስ ጀርባ ሌሎች ሓያላን ሐገራት ማለትም እነ አሜሪካ እንግሊዝና እስራኤል የመሳሰሉ ሓያላን ሐገራት አሉ ሲሉ በእርግጠኝነት እየተናገሩ ነዉ።

በእርግጥም ነገሩ እነሱ እንደሚሉት ባይሆን ኖሮ ኢመሬትሶች ከላይ የጠቀስናቸዉ ወደቦች አልበቃ ብሏቸዉ ሌሎች ተጨማሪ ወደቦችን ማለትም እነ አልመኻእን፣ አልሸጀርን እና አልመክላን ለመቆጣጠር ተጨማሪ ወታደራዊ ጉልበትን ባላባከኑ ነበር ከፍተኛ የሆነ ወጭም ባላወጡ ነበር ለማለት እንገደዳለን።

በክፍል አንድና ሁለት ዝግጅታችን ለማሳየት እንደሞከርነዉ የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስና ሳዑዲ ዐረቢያ ተናበዉ እና ተግባብተዉ የሚሰሩ የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ናቸዉ ብለን ነበር  ታዲያ እነዚህ ሐገራት ቀድሞዉንም ለጋራ ጥቅም የሚሰሩ ስለሆነ አንዱ በሌላዉ ላይ አይራመድም አንዱ በሌላዉ ላይ እንቅፋት አይሆንም እንዲያዉም አንዱ ለሌላዉ ሽፋን በመስጠት ተጠባብቀዉ ይሰራሉ እንጅ።

እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለዉ የሚገባ ነገር ሳዑዲ ዐረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ በቀይ ባህር ቀጣና እንዲሁም በአለማችን እጅግ እስትራቴጂክ በተባለለት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚያደርጉት መጠነ ሰፊ እንቅስቀሴ ለተቀናቃኞቻቸዉ ማለትም ለእነ ኳታርና ቱርክ ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸዉ አላደረገም በመሆኑም የእነ ሳዑዲን እንቅስቃሴ በአይነ ቁራኛ መከታተል ጀመሩ ከዛም አልፎ እነሱም በበኩላቸዉ እነ ሳዑዲ በማይነቀሳቀሱባቸዉ እና በእነሱ ስር ባልወደቁ ወደቦች አካባቢ መንቀሳቀስ ጀመሩ እናም እነሆ ከሱማሊያ እና ከሱዳን መንግስት ጋር ተቀራርበዉ ለመስራት እቅድ ማዉጣት ጀመሩ።

እናም እነሆ ኳታርም ለመጀመሪያ ጊዜ ከሐገሯ ወደቦች ወጣ ብላ በሱዳን እና ሱማሊያ ዉስጥ ወደቦችን አልምታ ለመጠቀም ከሱዳን እና ከሱማሊያ መንግስት ጋር መደራደር ጀመረች ተሳካላትም።

ኳታር የኢመሬትስን ወታደራዊ አይዶሎጂያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሩጫዎችን ገደብ ለማስያዝ በእርግጥም መንቀሳቀስ ጀመረች እናም አሁን በእስር ቤት ከሚገኙት ከዛኔዉ የሱዳን ፕሬዚደንት ከነበሩት ከዑመር አል በሽር ጋር ስምምነቶችን ተፈራርመዉ የሱዳን ወደቦችን የማልማት ስራም በይፋ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም እነ ዓብዱል ፈታህ አል ቡርሓን በ 2019 ባደረጉት መፈንቅለ መንግስት ምክንያት  እነሆ ፕሮጄክታቸዉ ተጨናግፎ ቀረ።

እናም የእነ ኳታር ፕሮጄክት መቀጠል አለመቀጠል ጉዳይ ከሱዳን ወቅታዊ ትርምስ ጋር አብሮ የሚታይ ነዉ የሚሆነዉ የሲቪሎች እና የምሁራን ንቅናቄ አይሎ ወታደራዊ መንግስቱ ከስልጣን የሚወገድ ከሆነ ኳታርና ቱርክ ሱዳን ዉስጥ ሊያሳኩት የፈለጉት እቅድ ይሳካል ካልሆነ ግን የቱርክ ባላንጣ የሆነችዉ ግብፅ ከአል ቡርሓን ጀርባ እስካለች ድረስ የኳታርና የቱርክ እቅድ ህልም ሆኖ ይቀራል እንጅ ሊሳካ እንደማይችል ከወዲሁ መገመት አያዳግትም።

ሱዳን ዉስጥ በ 2019 መፈንቅለ መንግስት ተደርጎ አልበሽር ከስልጣን ባይወገዱ ኖሮ የእነ ኳታርና ቱርክ እቅድ በሱዳን ትልቅ የተባለዉን የሰዋኪንን ወደብ አልምቶ መጠቀም ከዛም ቀስ በቀስ የጦር ሰፈራቸዉ የማድረግ ዓለማ ነበራቸዉ።

እንደሚታወቀዉ የኳታር መንግስት ከቱርክ መንግስት ጋር የአይዶሎጂና የጥቅም ዉህደት ፈጥሮ ዐረቦች ለኛ  ጠላት ናት ብለዉ ከሚያስቧት ከቱርክ ጋር ሆነዉ በዐረብ ሐገራት ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ ስጋት ፈጥራለች በሚል ሳዑዲ ዐረቢያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኢመሬትስ፣ ግብፅና በህሬን ኳታርን ከማግለልም አልፈዉ ማዕቀብ ጥለዉባት እንደነበረ ይታወሳል ታዲያ ኳታርም ለዚህ ተግባራቸዉ በአግባቡ ምላሽ መስጠት እንዲመቻት ልክ ኢመሬትስና ሳዑዲ በቀይ ባህር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ልክ ተጨባጭ የሆኑ ስራዎችን መስራት ጀመረች እናም ቀጣናችን የአፍሪካ ቀንድና የቀይ ባህር አካባቢ በሚያሳዝን መልኩ የጉልበት መፈታተሻ፣ የፉክክር ሜዳ፣ የአዳዲስ መሳሪያዎች መሞከሪያ እና የተለያዩ አይዶሎጂዎች ማራመጃ እና የዉድድር ሜዳ ሆነ።

ለማንኛዉም ኳታርና ቱርክ በጥምረት በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እና ወደፊት ለመተግበር ያቀዷቸዉ ዓላማዎች ገና ጀመርናቸዉ እንጅ አልተነኩም።

ስለሆነም ቱርክና ኳታር በሱማሊያ በሱዳንና በኤርትራ አካባቢ ምን ለማድረግ አቅደዋል? የሱማሊዋን ሆቢዮ ወደብ ለማልማት የታሰበዉ ለምንድነዉ? ቱርክ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታደርጋቸዉ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለቀጣናዉ ህዝቦች ያለዉ ፋይዳስ ምንድነዉ? ኳታር ከቱርክ ጋር በጥምረት ሆና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታሳያቸዉን የተቀናቃኝነት ስሜትስ እነ ኢመሬትስ እንዴት እያዩት ነዉ? የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸዉን ጉዳዮች በሚቀጥለዉ ሳምንት እንመለስባቸዋለን አስከዛዉ ሳምንታችሁ የስኬት እንዲሆን ተመኘሁ።

ዑመር መኮንን ነኝ። ከአባይ ጓዳ – ሰላም

Continue Reading

ዲፕሎማሲ

አዲሱ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስና የሓያላን ሐገራት ፉክክር – ክፍል ሁለት

Published

on

featured
Photo: Social Media

(ዛክ ፌርቲን ጽፎት ብሩኪንግ ዱሓ ማዕከል ያሳተመዉን እንደ ማጣቀሻ በመጠቀም የተፃፈ ተከታታይ ዝግጅት)

በባለፈዉ ሳምንት በክፍል አንድ ዝግጅታችን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ቀጠናዉ እጅግ ስትራቴጂክ በመሆኑ  የሓያላን ሐገራት ፉክክር እየታየበት የመጣ ቀጣና መሆኑንና የተለያዩ ጫናዎችም እያረፉበት መምጣቱን ተመልክተናል።

ከሓያላን ሐገራት በተጨማሪ የገልፍ ዓረብ ሐገራት በተለይም የሳዑዲ ዓረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኤርትራ እና በጅቡቲ የባህር በሮች አካባቢ የሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች አንድምታቸዉ ምንድነዉ? ንብረትነታቸዉ እዉቅና አልባ ለሆነችዉ ለሱማሌላንድ የሆኑትን የዘይላን እና የበርበራን ወደብ አጠቃቀም በተመለከተ እየታዩ ያሉ ፉክክሮችስ ምን አይነት መልክ አላቸዉ? ወደብ አልባዋ ሚስኪኗ ኢትዮጵያስ በሚያሳዝን የታሪክ አጋጣሚ የራሷ የባህር በር ባይኖራትም  ቢያንስ ያለ ስጋት የምትጠቀምበት ወደብ እንዲኖራት ምን እያሰበች ነዉ? የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸዉን ነገሮች ለማየት ለዛሬ ቀጠሮ ይዘን መለያየታችን ይታወሳል።

እነሆ ቀጠሯችንን አክብረን በሰዓታችን ተገኝተናል የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ ዑመር መኮንን ነኝ እሰከ ፕሮግራማችን ፍፃሜ አብራችሁን ሁኑ።

የአፍሪካ ቀንድ ሐገራት ማለትም ኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሊያ፣ ሱማሌላንድ፣ ፑንት ላንድና ምስራቅ ሱዳን ከገልፍ ዓረብ ሐገራት ጋር በቀይ ባህር የተሳሰሩ የጋራ ታሪክ ተመሳሳይ ባህልና ወግ እንዲሁም ማንነት ያላቸዉ ወንድማማች ሐገሮች ናቸዉ።

ሆኖም ቅኝ ገዢዎች ሐገራትን ለራሳቸዉ በሚመች መንገድ ሐገራትን እርስ በርስ እንዲከፋፈሉና አንዱ ከሌላዉ የተለዬ ማንነት ያ ማንነቱ ደግሞ በላጭ ማንነት ተወዳዳሪ ማንነት መስሎ እንዲታየዉ በማድረግ አነሆ ወንድማማች ህዝቦች ተያይተዉ ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳቸዉ ተናንቀዉና ተናቁረዉ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

ከሌሎች የገልፍ ዓረብ ሐገራት በተለዬ መልኩ በአፍሪካ ቀንድ እና በቀይ ባህር አካባቢ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ በማድረግ የምትታወቀዉ የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ ናት።

ኢመሬትሶች እንደሚሉት ከሆነ በቀይ ባህር እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምናደርጋቸዉ እንቅስቃሴዎች ተፈጥሯዊ ብቻ ሳይሆኑ ብሔራዊ ጥቅማችንም ያለዉ እዚሁ አካባቢ ነዉ ብለዉ ያምናሉ።

ሆኖም ይህ እንቅስቃሲያቸዉ ከ 2015 ጀምሮ ራሳቸዉ ኢመሬቶች ጠልቀዉ በገቡበት የየመን ጦርነት እና በኳታር ከፍተኛ ፉክክር ምክንያት እየቀነሰ መምጣቱን መምጣቱን ማስተዋል ይቻላል።

በእርግጥ እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለዉ የሚገባ ነገር የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስን የሚያሳስባት በአፍሪካ ቀንድና በቀይ ባህር አካባቢ የኳታር ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ መምጣት ሳይሆን ከኳታር ጀርባ ያለዉ የቱርኮች ጠንካራ ፍላጎት ነዉ ለዚህም ነዉ እዚህ አካባቢ ያለዉ ፉክክር ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩንና ቅርፁን እየቀያየረ እያየለ የመጣዉ።

ምንም እንኳን የኤርትራዋን የአሰብ ወደብ ኢመሬቶች ከ 2015 ጀምሮ መጠቀም የጀመሩት በሳዑዲ ዓረቢያ አቀራራቢነት ቢሆንም ኢመሬትስ ግን ይህንን አጋጣሚ እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም በቀጣናዉ ያላቸዉን ተፅእኖ ከፍ ለማድረግና በአካባቢያችን ያላቸዉን እንቅስቃሴ ለማስፋት እየተጠቀሙበት ነዉ።

የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ በየመን ሁሲዎች ላይ የወሰዷቸዉ  የባህር እና የአየር ላይ ጥቃቶች ከቀይ ባህር ከኛዋ የኤርትራ ወደብ ከአሰብ መሆኑ ደግሞ ለቀጣናዉ አለመረጋጋት እና የፀጥታ ችግር አይነተኛ ሚና ነበረዉ።

በባለፈዉ ሳምንት ዝግጅታችን ሳዑዲ ዐረቢያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ ተናበዉ እና ተግባብተዉ የሚሰሩ እንደመሆናቸዉ መጠን ኤርትራ ዉስጠም ቢሆን ተናበዉ እየሰሩ መሆኑን መረጃ ማጣቀስም አያስፈልግም ።

ምንም እንኳን ኤርትራ ብታስተባብለዉም ኢመሬቶች የኤርትራን አሰብ ወደብ ለ 30 ዓመት ኮንትራት ይዘዉታል መባሉ አንድም የኤርትራንና የኢመሬትን ጠንካራ ግንኙነት የሚያሳይ ሲሆን ሁለትም ኢመሬትስ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ምን ያህል ስር እየሰደደች መምጣቷን ቁልጭ አድርጓ ያሳየናል።

በተለይ ደግሞ ኢመሬቶቾ በአሰብ ወደብ ላይ ድሮኖችን ጨምሮ ያስቀመጧቸዉ ዘመናዊ መሳሪያዎች በእርግጥም እዚህ በቀጣናችን እየታዬ ያለዉ ፉክክር ለሰላም ነዉ ? ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል።

ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ በየመን ሁሲዎች ላይ የሚያደርጓቸዉ ወታደራዊ ጥቃቶች ሐይማኖታዊ ይዘት ያላቸዉ ስለሆነ የጅቡቲን ወደቦች ተጠቅመዉ ጥቃት ለመፈጸም ያደረጓቸዉ ሙከራዎች ሁሉ ተቀባይነትን አላገኙም ስለሆነም የኤርትራን ወደብ አሰብን ከመጠቀም ዉጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ አላገኙም ታዲያ ኤርትራም ይህንን ጥያቄ በሁለት ጠንካራ ምክንያቶች ለመቀበል ተገዳለች:-

  • አንደኛ   ኤርትራ ይህን በማድረጓ ለኤርትራ ከፍተኛ የሆኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች ስለሚሰሩላት ሲሆን
  • ሁለተኛዉ ደግሞ ኤርትራ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተገልላ የነበረች ሐገር በመሆኗ ኤርትራ ዳግም ስመ ጥር ሆና የራሷ ሚና ያላት ሐገር መሆኗን ለማሳየትም እድል ስለሚሰጣት ነዉ።

ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የአሰብንም ሆነ ሌላኛዉን የምፅዋ ወደብ ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድ ግዛት በነበረችበት ጊዜ የራሷ ወደቦች ነበሩ ሆኖም በመጥፎ ታሪካዊ አጋጣሚ ሁሉም ወደቦች ከኤርትራ ጋር ሲገነጠሉ የአሰብን ወደብ በኪራይ መልክ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እ.ኤ.አ በ 1998 እስከፈነዳበት ድረስ ስትጠቀምበት ኖራ ነበር።

ሆኖም በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል በተደረገ እጅግ ዘግናኝ ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ለ 30 ዓመት ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ ከአሰብ ወደብ ተባራ የጅቡቲን ወደቦች እንደ ዋነኛ የባህር በሮቿ መጠቀም ጀመረች።

አሁን አሁን ማለትም ከለዉጡ በኋላ በአብይ አሕመድና በኢሳያስ አፈወርቂ መካከል በተፈጠረ ጠንካራ ግንኙነት ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ የመጠቀም ፍላጎት ቢያድርባት እንደ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ኢመሬትስና ኢትዮጵያ ባላቸዉ ጠንካራ ግንኙነቶች ምክንያት ሁኔታዎች ሁሉ ምቹ ናቸዉ።

የኢመሬትስ እንቅስቃሴ በዚህ አላቆመም ወዲህ ሱማሌላንድም በመምጣት የበርበራን ወደብ አልምቶ ለመጠቀም በ 2016 የዱባዩ ዓለም አቀፍ የወደቦች አስተዳደር ድርጅት ጨረታዉን በማሸነፉ እሰከ 2018 ድረስ የማስፋፊያ ስራዎችን ሰርቶ ጨረሶ በስራ ላይ እንዲዉል አድርጓል።

ከዚሁ በአፍሪካ ቀንድ ከሚታዩ ፉክክሮች መካከል እንደ ማሳያ የሚሆነዉ የተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ ወደቦችን ለወደብነት ብቻ ሳይሆን ግዙፍ ግዙፍ የሆኑ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮችንም በአካባቢዉ ለመገንባት ደፋ ቀና ሲሉ መታየታቸዉ ነዉ ስለሆነም ይህ አይነት ተግባራቸዉን ያልወደዱት የሱማሌላንድ ዜጎች ድርጊቱን ተቃዉመዉት እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያ እና በተባበሩት ዓረብ ኢመሬትስ መካከል ያለዉ ግንኙነትና የጋራ ጥቅሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ መምጣታቸዉን ከሚያመላክቱ ማስረጃዎች መካከል ኢመሬትሶች በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የኢትዮጵያን አጋርነት መፈለጋቸዉ ነዉ።

ኢመሬትስ በሱማሊላንዷ በርበራ ወደብ በምታደርገዉ እንቅስቃሴ በበርበራ ወደብ ላይ 51 % የዱባይ 30 % የሱማሌላንድ ሲሆን 19 % ደግሞ የኢትዮጵያ ነዉ።

ከዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ሳንወጣ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ በማንም ተፅእኖ ስር ያልወደቀ ወደብ ለማግኘት ከሱማሌላንድ ጋር እየተነጋገረች መሆኑን በርካታ ምንጮች እየገለፁ ነዉ።

በተለይ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ለመፈራረም ኢትዮጵያ ላይ ታች እያለች ነዉ ሆኖም ግን ይህን የኢትዮጵያን እንቅስቃሴ አንዳንድ ለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት የሌላቸዉ አካላት አወንታዊ ትርጉም እየሰጡት አይደለም።

ኢትዮጵያ እዉቅና የሌላትን ሱማሌላንድን ልትወር ነዉ፣ ኢትዮጵያ የባህር ሓይል የምታሰለጥነዉ ሱማሌላንድን ልትወር ነዉ፣ የአብይ አሕመድ ህልም ረጅም ነዉ፣ ኢትዮጵያ በርበራን ድሮም ቢሆን የምንጠቀምበት በሐረር ክፍለ ሐገር አማካኝነት እኛ ነበርን እያለች ነዉ፣ በርበራ ባለቤት የሌለዉ ወደብ ነዉ የሚሉና ሌሎች ተራ አሉባልታዎችንም በቅርቡ ስንሰማ ነበር ደግነቱ ግን የሱማሌላንዱ ፕሬዚደንት ወደ ኢትዮጵያ መጥተዉ የወደብ አጠቃቀምን ጨምሮ በሌሎች ሁለትዮሽ ጉዳዮች ዉጤታማ ዉይይት ማድረጋቸዉን መግለፃቸዉ ገላገለን እንጅ።

የሆነዉ ሆኖ አሁን መነሳት ያለባቸዉ ጥያቄዎች በሚያሳዝን የታሪክ አጋጣሚ ወደብ አልባ ዝግ የሆነችዉ ኢትዮጵያ ወደብ ሊኖራት የሚችለዉ በምን አይነት ሁኔታ ነዉ? የኢመሬቶች እዚህ አፍንጫችን ስር ድረስ መጥተዉ አንዴ ኤርትራ ላይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጅቡቲ ላይና ሱማሌላንድ አካባቢ የሚያደርጓቸዉ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለኢትዮጵያ ያላቸዉ ፋይዳ ምንድነዉ? ኢትዮጵያ እራሷን ችላ የምታስተዳድረዉ ወደብ አያስፈልጋትም ወይ? ከዉጭ ሊቃጡባት የሚችሉትን የበህር ላይ ዉጊያዎችንስ እንዴት ነዉ መመከት ያለባት? የኢመሬትስና የኢትዮጵያ ወዳጅነትና አጋርነትስ አስከ የትና አስከ ምን ድረስ ነዉ? እንደ ሳዑዲ ዐረቢያና የተባበሩት ኢመሬትስ ያሉ የገልፍ ዓረብ ሐገራት ቀይ ባህርን ተሻግረዉ በዚህ መልኩ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ካደረጉ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ማንነቷ ከቀጣናዉ ጋር በእጅጉ የተቆራኘዉ ኢትዮጵያስ ምን ማድረግ ይጠበቅባታል?

እነዚህን ወሳኝ እና እንቅልፍ የሚነሱ ጥያቄዎች ለመመለስ መንግስት እንደ መንግስት በፅኑ ሊያስብባቸዉ የሚገባ ቢሆንም ለመንግስት ብቻ የሚተዉ እንዳልሆኑ ደግሞ ልብ ልንል ይገባል።

ዞሮ ዞሮ ኢመሬቶችና ሳዑዲዎች በቀይ ባህር አካባቢ የሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች ከጀርባቸዉም ማንም ይኑር ማን ከሱማሌልድ እና ከኤርትራ ወደቦች በተጨማሪ ፑንትላድም አካባቢ እንቅስቃሲያቸዉን አጠናክረዉ ቀጥለዉበታል ስለሆነም የእነዚህ ሐገራት እንቅስቃሴ ዳራዉ ምንድነዉ? ኢመሬትስ እና ሳዑዲ በአንድ በኩል የመን በሌላ በኩል ያላቸዉ ቁርሾና አለመግባባትስ መንስኤዉ ምንድነዉ? የእነሱ ፉክክር በእኛ ሜዳ ላይ መሆኑስ የሚያሳድረዉ ተፅእኖ ምንድነዉ? ከአፍሪካ ቀንድ ሐገራት መሪዎችስ ምን ይጠበቃል? የሚሉትን ጥያቄዎች በቀጣይ ሳምንት እንመለከታቸዋለን አስከዛዉ መልካም ሳምንት።

ሰላም

በ ዑመር መኮንን

Continue Reading

ዲፕሎማሲ

አዲሱ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ እና የሓያላን ሐገራት ፉክክር – ክፍል 1

Published

on

featured
Photo: Social Media

(ዛክ ፌርቲን ፅፎት ብሩኪንግ ዱሓ ማዕከል ያሳተመዉን እንደ ማጣቀሻ በመጠቀም የተፃፈ ተከታታይ ዝግጅት)

ከአምስት አመት ወዲህ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየታዩ ያሉት ፉክክሮች ጤናማ አይደሉም አንድም ለቀጣናችን ሁለትም ለአፍሪካችን ተስፋን የሰነቁ ሳይሆኑ በርሓብ ላይ ርሓብን በጦርነት ላይ ጦርነትን በችግር ላይ ችግርን የሚያክሉ እየሆኑ ነዉ።

በርካታ ምሁራን በተለያዩ ጥናታዊ ፅሑፎቻቸዉና ምሁራዊ ትንታኒያቸዉ እንደሚናገሩት ከሆነ ለአፍሪካ ቀንድ መተራመስ ዋነኛ ምክንያት ታላቁ  የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመር ነዉ ይላሉ።

ምንም እንኳን የህዳሴዉ ግድብ በታችኛዉ ሐገራት ላይ ምንም አይነት ጉዳት እንደሌለዉ እየታወቀ ግብፅ በምታራምደዉ የምቀኝነት፣ የሴራና የህፃንነት ፖለቲካ ምክንያት ግድቡ የግብፅ ሚዲያዎች በሚያራግቡት የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የተዛባ መረጃ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲደርስ ቢደረግም እዉነታዉ ግን እንዲያዉም ግድቡ ለታችኛው ተፋሰስ ሐገራት በተለይም ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።

የሆነዉ ሆኖ የግብፅ የሴራ ፖለቲካ በግብፅ ሚዲያዎች ተከሾኖ ለዓለም በመቅረቡ ምክንያት እነሆ የአፍሪካ ቀንድ በባሰ ትርምስና ዉጥንቅጥ ዉክጥ ይገኛል።

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የነበረዉ ደም አፋሳሽ ጦርነት፣ በሱማሊያ ዉስጥ የአል ሸባብን እንቅሰቃሴ ተከትሎ በቀጣናዉ እስካሁን ድረስ ጠባሳዉ ያልጠፋዉ ግጭት፣ በጅቡቲና ኤርትራ መካከል አልፎ ሲታዩ የነበሩ ግጭቶች፣ በኤርትራ እና በየመን መካከል በሐኒሽ ደሴት ዙሪያ ተከስቶ የነበረዉ ግጭት፣ በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል እስካሁኑ ሰዓት ድረስ የዘለቀዉ ዉጥረት፣ የኢትዮጵያን የዉስጥ ችግሮች ለማባባስ እና ኢትዮጵያን የማፍረስ እንቅስቃሴዎች ሁሉም ጀርባቸዉ ሲፈተሽ የግብፅ እጆች ፍንትዉ ብለዉ ይታያሉ ለዚህም ማሰረጃ ለማቅረብ ርቀን ሳንሔድ የግብፅ ሚዲያዎች ግብፃዊያን ምሁራንን ባለስልጣናትንና ፖለቲከኞችን ዋቢ አድርገዉ በየቀኑ የሚሰሯቸዉን ዘገባዎች መመልከት በቂ ነዉ።

አሁን አሁን ደግሞ በቀይ ባህር የቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙና የራሳቸዉ የባህር በር ያላቸዉ የገልፍ ሐገራት ሳይቀሩ በቀይ ባህር አካባቢ የሚያሳዩት ፉክክርና አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነቶች እዉን የቀጣናቸዉንና የቀጣናችንን ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት? ወይስ የሶስተኛ ወገን አጀንዳ ይዘዉ መጥተዉ ነዉ? ብለን እንድንጠይቅ እያደረገን ነዉ።

ግብፆች ባለፉት ሁለት ዓመታት የአባይ ጠባቂዎች በሚል ከሱዳን ጋር በጥምረት ያካሔዷቸዉ የጦርነት ልምምዶችስ እዉን አባይን ለመጠበቅ ወይስ ቀጣናዉን ለማተራመስ? እነሱ እንደሚሉት የጦርነት ልምምዳቸዉ አባይን ለመጠበቅ ከሆነ የአባይ እናትና አባት የሆነችዉ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት ልምምድስ ፋይዳዉ ምን ይሆን የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ እያስገደደን ነዉ።

የቀጣናዉን እንቅስቃሴ በአንክሮ ለሚከታተል ሰዉ በእርግጥም እነ ሳዑዲ ዓረቢያ ኢመሬትስ እና ቱርክንም ጨምሮ በቀይ ባህር አካባቢ የየራሳቸዉን ጦር ሰፈር ለመገንባት ጥረቶችን ሲያደርጉ እያስተዋልን ነዉ።

በእርግጥ ከቀይ ባህር ሐገራት በተለይም ከአፍሪካ ቀንድ ሐገራት መካከል ጅቡቲን ብንወስድ ሓያላን ሐገራት የጦር ሰፈር ገንብተዉ ከፍተኛ ፉክክር የሚያደርጉባት ሐገር መሆን ከጀመረች ሰነባብታለች።

ቻይና ፣ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና አሜሪካ በጅቡቲ የየራሳቸዉን የጦር ሰፈሮች ገንብተዉ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሐብት በኢንቨስትመንት ስም ወይም የየራሳቸዉን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚል ሽፋን ጤናማ ያልሆነዉን ፉክክራቸዉን በማጧጧፍ ላይ ናቸዉ።

ታዲያ ይህን የተመለከቱ እነ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኢመሬትስ፣ ኳታርና ቱርክም የየራሳቸዉን ጦር ሰፈር በጅቡቲ ወይም የባህር ባላቸዉ የአፍሪካ ቀንድ ሐገራት አካባቢ (ኤርትራ፣ ሱማሊያ፣ ሱማሊላንድና ፑንት ላንድ) አካባቢ ለመገንባት የሚያስችላቸውን ስምምነት ለመፈራረም ሩጫዉን ተያይዘዉታል።

እጅግ የሚገርመዉ ደግሞ ከዚህ በፊት እንቅስቃሲያቸዉ በህቡእ እንጅ እምብዛም በይፋ ሲንቀሳቀሱ የማይታዩ እንደነ እስራኤልና ህንድ ያሉ ሐገራትም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መስተዋሉ ነዉ።

አብራሓም በሚል ስያሜ የሚታወቀዉን የስምምነት መረብ ሽፋን በማድረግ ኢስራኤል ከዓረብ ሐገራት ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ለማጠናከር ደፋ ቀና ስትል ቆይታለች እንቅስቃሴዋም የተሳካ ነበር ለማለት ይቻላል።

ይህ የአብራሓም ስምምነት አሁን አሁን ደግሞ የቆዳ ስፋቱን በመጨመር ለበርካታ ሺ ዓመታት በፀረ እስራኤል አቋሙ የሚታወቀዉን ሱዳንንም ለማጠቃለል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ቆይቶ እነሆ ሱዳንም የዚህ ስምምነት አንዱ አካል ለመሆን በቅቷል።

የእስራኤል ሱዳንን ግንኙነት ለማጠናከር እና ባልተጠበቀ መልኩ ግንኙነታቸዉ በዚህ መልኩ እንዲሆን የማቀራረቡንና የማስማማቱን  ከፍተኛ ስራ የሰሩት እነ ኢመሬትስ ሳዑዲ ዓረቢያ እና በሕሬን መሆናቸዉን ልብ ይሏል።

ከአሜሪካ ጋር የቆየ ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ፉክክር በማድረግ የምትታወቀዉ ሩስያም ብትሆን በቀጣናዉ የምታደርገዉ እንቅሰቃሴ ተፅእኖ ፈጣሪ እንደሆነ ለማስተዋል ብዙ ጉልበት አይጠይቅም።

ሩስያ ለአፍሪካ ቀንድ ሐገራት የምታደርጋቸዉ ወታደራዊ ድጋፎች በጣም ከፍተኛ ናቸዉ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያሉ ሐገራት ፀረ አሜሪካ አቋም ይኖራቸዉ ዘንድ የሩስያ ምኞትና ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሩስያ ጊዜዋንም ጉልበቷንም ገንዘቧንም ሳትሰስት የምትዋደቅለት ዓላማዋ ነዉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የአሜሪካዉ Foriegn Affairs መጽሔት በ 2019 እትሙ እንደፃፈዉ ከሆነ የገልፍ ዐረብ ሐገራት በአፍሪካ ቀንድ በቀይ ባህር አካባቢ አደገኛ ጨዋታ እየተጫወቱ ነዉ ሲል አስነብቦናል።

አንድ በ 2018 የወጣ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ ከሆነ ደግሞ ሓያላን ሐገራት የገልፍ ዐረብ ሐገራትንና ሌሎች የኤስያ ሐገራትን ማለትም ቱርክን ሩስያንና ህንድን ጨምሮ በቀይ ባህር አካባቢ የሚያደርጉት ፉክክር ጤናማ እንዳልሆነ አረጋግጦ የሰራዉ በኢትዮጵያ ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሱማሊያ፣ ሱማሌላንድ፣ ሱዳን ፣ ኢመሬትስ፣ ሳዑዲዓረቢያ፣ ኳታር ፣ ቱርኪያ ፣ አሜሪካ የሚገኙ ምሁራንን እና ፖለቲከኞችን አነጋግሮ እንደሰራዉ ይፋ አድርጓል።

ከገልፍ ሐገራት መካከል በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ረጅም እጅ እንዳላት የሚመሰክርላትና በቀጣናዉ ጉልህ ሚና አላት የሚባልላት ኢመሬትስ በቀጣናዉ እዚህም እዛም እየታየች ነዉ።

ምንም እንኳን እንደነ ፕሮፌሰር ሐሰን መኪ ያሉ ሱዳናዊያን ምሁራንና የታሪክ ተመራማሪዎች ኢመሬትስ እና ኳታር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች ተፈጥሯዊ አይደሉም፣ ከአቅማቸዉ በላይ ናቸዉ፣ እነሱን አይመጥኑም፣ የሶስተኛ ወገን ጥቅም ለማስከበር ነዉ ቢሉም ተጨባጩና በአይናችን በብረቱ እያየነዉ ያለዉ ነገር የሚመሰክረዉ ግን ኢመሬትስም ሆነች ሳዑዲ ዐረቢያ ቱርክም ሆነች ኳታር በቀጣናዉ ትኩረት የሚስብ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ነዉ።

ከለዉጡ ወዲህ ማለትም ከዶ/ር አብይ አሕመድ ስልጣን ላይ መዉጣት ወዲህ ኢመሬትስ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነት ከቀን ወደ ቀን እየተጠናከረ መጥቷል ። ነገሩ ያላማራት ግብፅ በኢመሬትስ ላይ ከፍተኛ የሆነ የስነ ልቦና ዘመቻ ጀምራባት እንደነበረም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ሲሆን በዐረብ ሊግ አማካኝነትም ለማሳጣት ጠንክራ ሰርታለች።

በዚህም የተነሳ ግብፆቾ ኢትዮጵያ ዉስጥ ኢንቨስትመንት እያካሔደ ያለ ማንኛዉም ዐረብ የኢትዮጵያን ህዳሴ ግድብ እንደደገፈ ይቆጠራል ብለዉም በኢትዮጵያ መዋለንዋያቸዉን አፍስሰዉ እየሰሩ ያሉ የዓረብ ሐገራትንም ለማሸማቀቅ ሞክረዉ ነበር የሚሰማቸዉ ጠፍቶ እንጅ።

በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ብሎም ከአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ የአይንና የአፍንጫ ያህል ናቸዉ በሚባለዉ በደቡብ አረቢያን እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢም ኢመሬትስ የተለዬ ሚና አላት።

ኢመሬትስን ወደ ቀጣናዉ የገፋፏት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉ እነሱም አንደኛዉ በ 2015 በየመን የተቀሰቀሰው ጦርነትና የእርሷ ዋና ተዋናይነት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ በቱርክ ታግዛ በቀጣናዉ ሌላ ፉክክር በማድረግ ላይ የምትገኘዉን ኳታርን ለመቀናቀን ብሎም የእነ ቱርክን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለማስቆም ነዉ።

እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለዉ የሚገባ ነገር አለ እሱም ኢመሬትስና ሳዑዲ ዓረቢያ ፀረ ቱርክ አቋም ይዘዉ የእነ ኳታርንና የእነ ቱርክን እንቅስቃሴ ለማስቆም ተናበዉ እና ተደጋግፈዉ የሚሰሩ የአንድ ሳንቲም ግልባጮች መሆናቸዉን ነዉ።

ስለሆነም ሳዑዲ ዐረቢያ በአፍሪካ ቀንድ የምታደርገዉን እንቅስቃሴ አንዳንዴ ከኢመሬትስ ጋር በመቀናጀት የምትፈጽመዉ ሲሆን ሌላ ጊዜ ደግሞ በተናጠልም ልታደርገዉ ትችላለች ኢመሬትስም እንዲሁ ይህን ብታደርግ ለሳዑዲ ዐረቢያ ስጋት አይሆንም።

ለመሆኑ የሳዑዲ ዐረቢያ እና የኢመሬትስ ጥምር እንቅሰቃሴ በኤርትራ ያላቸዉ የንግድ የወታደራዊና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ምን ይመስላሉ? የበርበራንና የዘይላን ወደብ ለመጠቀም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እና የወደብ አልባዋ የሚስኪኗ ኢትዮጵያ ሚናስ ምንድነዉ? የሚሉትንና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸዉን ጉዳዮች በሚቀጥለዉ ሳምንት የምንመለከታቸዉ ይሆናል እስከዛዉ ቸር ሰንብቱ።

ዑመር መኮንን ነኝ ከአባይ ጓዳ።

Continue Reading

በብዛት የተነበቡ