ለወትሮውም እንደሚነገረው አሜሪካ በየቦታው ነገር እየተነኮሰችና እየተናከሰች ዱካዋን ማጥፋቱን ታውቅበታለች በሚል ትብጠለጠላለች፡፡ ዛሬም ያደረገችው ያንኑ ነው፡፡ በባልካን ቀጣና ከዩክሬን ጋር አብራ በሩሲያ ላይ ምዕራባውያን አጋር ወዳጅ ሥትል አስተባብራ ውረድ እንውረድ ሥትል ሩሲያም ለዚያ የአሜሪካ መራሹ የምዕራባውያን ጥምረት ለአፀፋ ምላሽ ስትሰናዳ አሜሪካ ዛሬ በደቡብ ቻይና ባህር ሌላ አሣት የማንደዷ ነገር ተሰምቷል፡፡
አሜሪካ በደቡብ ቻይና ባህር ግዙፍ የተባለለት የባህር ላይ የጦር ልምምድ መጀመሯን ከወደዚያው የሚወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡ በአሜካ የባህር ኃይል የቻይና ባህር የጦር ልምምድ ዙሪያ ትንታኔያቸውን የሚያቀርቡ አካላትም ጉዳዩ ግልፅ ነው አሜሪካ ከሩሲያም ከቻይናም ጋር ወደ ማይቀር ጦርነት ትገባለች ነው የሚሉት፡፡
ሁለት የግዙፍ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚዎቹ USS ካርል ቪንሰንና USS አብርሃም ሊንከን እንዲሁም ሌሎች የጦር መሣሪያዎች የተካተቱበት የባህር ኃይል የጦር ልምምድ የተጀመረው በባለፈው እሁድ መሆኑ ታውቋል፡፡ አሜሪካ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠችው ማብራሪያም ቢሆን የባህር ኃይሏን የማጠናከርና የውጊያ ብቃቷን ለማረጋገጥ መሆኑን ነው ያስታወቀችው፡፡
የአሜካ የጦር መርከቦች የባህር ላይ የጦር ልምምዳቸውን የሚያደርጉትበ በተለይ በሃይናን ደሴት ላይ መሆኑ ነው የተገለፀው፡፡
የሃይናን ደሴት በደቡብ ቻይና ባህር የምትገኝ ቁልፍ የባህር ኃይል ማዘዣ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ባለፈው ሣምንት በሳውዝ ቻይና ሞርኒግ ፖሥት ላይ የወጣው ጽሑፍ እንደሚያሳየው የአሜሪካዎቹ የጦር አውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከቦች ባለፈው የአውሮፓውያኑ የ2021 ዘመን ብቻ በደቡብ ቻይና ባህር አሥር ጊዜ መግባታቸውን አሳይቷል፡፡ የአሜሪካ የጦር መርከቦች በፈረንጆቹ 2020 ስድስት ጊዜ በ2019 ደግሞ አምስት ጊዜ በደቡብ ቻይና ባህር ዘልቀው መግባታቸው ይታወሣል፡፡
የአሜሪካ የጦር መርከቦች በተለይም USS ካርል ቪንሰን ከዚህ ቀደምም በአወዛጋቢው የደቡብ ቻይና ባህር በምትገኘው የሥፕራትሊ ደሴት የ5 ቀናት የባህር ላይ የጦር ልምምድ ማድረጓ አይዘነጋም፡፡ ባለፈው ሣምንት የአሜሪካዎቹ USS ካርል ቪንሰንና የኤሴክስ አምፊቢየሥ የጦር መርከቦች ከአብርሃም ሊንከኗ የጦር መርከብ ጋር በፊሊፒንስ ባህር የጦር ለምምድ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
ያ ሥፍራ ደግሞ ከታይዋን ደሴት በስተ-ምሥራቅ አቅራቢያ የሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡ የአሜሪካ የጦር መርከቦች በፊሊፒንስ አዋሳኝ የውሃ ክልል ላይ ባደረጉት የጦር ልምምድ በሁለት ጃፓን የጦር መርከቦች አጃቢ ማግኘቱ ይነገራል፡፡ ሁለቱ የጃፓን የጦር መርከቦች JS Hyuga እና JS ሚዮኮ የሚባሉት ናቸው፡፡
ያ የአሜሪካ በደቡብ ቻይና ባህር የባህር ላይ የጦር ልምምድ ማድረግ ታዲያ አሜሪካ ከቻይና ጋር ወደ ጦርነት ብትገባ በቻይና ቁጥጥር ስር ላሉት ደሴቶችና ለቻይና ዋናው ምድር ሣይቀር ሙሉ በሙሉ ለጥቃት የተጋለጠ መሆኑን አመላካች ነው፡፡
የአሜሪካ የመገናኛ ብዙኃን ባሰራጩት ዘገባ የሚያናፍሱት ጭብጥ ቢኖር የአሜሪካን የባህር ላይ የጦር ልምምድ ሣይሆን የቻይናን ምላሽ የተመለከተ መሆኑ ይገለፃል፡፡ ቤጂንግ ታይፔይን ለመውረር አቆብቁባ እየጠበቀች መሆኑ በስፋት ይነገራል፡፡ አሜሪካ ደግሞ ታይዋን እንድትነካ ያለመፈለጓን በተደጋጋሚ ከመግለፅ ባሻገር የግዙፍ ቢሊዮኖች ዶላር የጦር መሣሪያ ሺያጭና የሥልጠና ድጋፍ ለታይዋን እያደረገች መሆኑ ይታወቃል፡፡
የታይዋን ባለሥልጣናት በምሬት እንደሚገልፁት ባለፈው እሁድ 93 የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በታይዋን የአየር ክልል ጥሰው መግባታቸውንና በማግሥቱ ሰኞም 13 የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በተመሣሣይ ወደ ታይዋን የአየር ክልል መግባታቸውን ይናገራሉ፡፡
የአሜሪካ የጦር መርከቦች በደቡብ ቻይና ባህር ላይ የጦር ልምምድ ሲያደርጉ በውሃ አካላት ላይ በነፃነት የመዘዋወር መብት መሆኑን የታይዋንና የአሜሪካ ሹማምንት ይስማሙበታል፡፡
ይሁንና የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በዚያ የደቡብ ቻይና ባህር ላይ የሚበሩ ከሆነ ታይዋንን የመውረር ዝግጅትና ዛቻ ተደርጐ በምዕራባውያኑ የመገናኛ ብዙኃን በስፋት ይናፈሣል፡፡
ያ የታይዋን የአየር ክልል ተብሎ የሚጠራው ስፍራ በዓለማቀፍ ህግ ግልፅ የሆነ ቋሚ ማቀፊያ የለውም ነው የሚባለው፡፡ ዋሽንግተን በወቅታዊነት በሩሲያና በዩክሬን በያዘችው አቋም ተመሣሣይ በቻይናና በታይዋን ጉዳይም አንድ የሆነ አቋም ትገልፃለች፡፡
የሩሲያ ጦር በገዛ የሩሲያ ድንር ክልል የመስፈሩ ነገር በዩክሬን ላይ ወረራ ለመፈፀም የታቀደ ስልት ሆኖ ይምነዘራል፡፡ ያ ጉዳይ ታዲያ ዋሺንግተን የሞስኮውን ወኔ አሸማቃ በምሥራቅ አውሮፓ የበላይነቱን ለመጠቅለል የተሰላ ቁማር መሆኑ ይነገርለታል፡፡
አሜሪካ ከባለፈው እሁድ በደቡብ ቻይና ባህር የጀመረችው የባህር ላይ የጦር ልምምድ በUSS ካርል ቪንሰን የባህር ዕዝ ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ዳን ማርቲን ማብራሪያ በቻይና ኃይሎች ላይ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ባለፈው ሣምንት አውስትራሊያ ሲድኒ ውስጥ መግለጫ የሰጡት የብሪታንያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዛ ትሩሥ ቻይና በዩክሬን የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር ተተግና ታይዋንን ለመውረር ተዘጋጅታለች ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ሩሲያ በዚህ ወቅት ከምንጊዜውም በላይ ከቻይና ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑ ይነገራል፡፡
የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሊዛ ትሩስ በሰጡት ማብራሪያ ወራሪዎች ሀገራትን ለመውረር ሥ ጊዜን ይጠብቃሉ ነው ያሉት፡፡ ፋይናንሺያል ታይምስ ባለፈው ሣምንት ባወጣው ፅሑፍ ሩሲያና ቻይና አዲስ የዓለም ስርዓት ሊዘረጉ ነው ሲል ማሰራጨቱ ይታወቃል፡፡
አሁን አሜሪካ ዐይኗን ያፈጠጠችባት ሩሲያ ለጦርነት ሥጋት ሲነገርባት በደቡብ ቻይና ባህር ዞራ አሜሪካ የጀመረችው የባህር ላይ የጦር ልምምድ የሚያሳየው ጦርነቱ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሊፈነዳ እንደሚችል ነው፡፡
ያ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ድፍን ዓለም በአፋጣኝ ወደ አጥፊ ጦርነት ውስጥ ትገባለች ለዚያውም ጦርነቱ የኑክሌር ጦርነት ነው የሚሆነው በሚል ስጋት ጋርጧል፡፡ ይህ በንዲህ እንዳለ ሩሲያና ቻይና በአረብ ባህር የጋራ የጦር ልምምድ መጀመራቸው ታውቋል፡፡
ሩሲያ ከቻይና ጋር ከምታደርገው የባህር ላይ የጦር ልምምድ ውጪም በእስያ ካሉ ህንድን ከመሣሰሉትና ከኢራንም ጋር የባህር ኃይል የጦር ልምምድ ማድርጓ ይነገራል፡፡ በተያዘው የፈረንጆቹ 2020 የአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በአረብ ባህር የጦር ልምምድ የሚያደርጉት ሩሲያና ቻይና ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ዕለት ልምምዳቸውን መጀመራቸው ታውቋል፡፡
ከሩሲያ የመከላከያ ሚኒስትር በወጣው መግለጫ እንደተመለከተው በባህር ላይ የጦር ልምምዱ የሩሲያ የፓስፊክ ዕዝና የሚሣይል ተኳሾቹ የክሩይዘር ቨርያግ እንዲሁም በርካታ የጦር ጀልባዎች ይሣተፋሉ ነው የተባለው፡፡
የቻይና የባህር ኃይል ደግሞ በሚሣይል አውድሞቹ የኡሩምቺና ታይሁ በተሰኙት የጦር መርከቦች መወከሉ ነው የተነገረው፡፡
እንደዚህ የኃያላኑ ፍጥጫ ከወዲያና ከወዲህ እሣቱ ሲራገብ ሸምጋይ ገላጋይ ብቅ የሚል የለም፡፡ የሰው ልጅ የሚኖርበትን ምድር ለማጥፋት አውቆትም ይሁን ሣያውቀው በሚያደርገው ጥድፊያ ራሱም የዚያ ጥፋት ሰለባ ስለመሆኑ ቆም ብሎ ያለማስተዋሉ ያጠያይቃል፡፡
ለትንታኔ ዘገባው በዋቢነት አልጀዚራ፣ ሲ.ኤን.ኤን፣ ሬውተርስና አዣንስ ፍራንስ ፕሬስን ተጠቅመናል፡፡
የዘገበው፡- ትዕግሥቱ በቀለ