Connect with us

ስነ ልቦና

አሁኑኑ ራስህን ፈልግ.. ዙሪያህንም አስስ..  ሰዉ ሁን

Published

on

featured
Photo: beyondphilosophy.com

መቼም ሰው ሁሉ እንዳስቀመጡት ማግኘት እንደ ገተሩት ግኡዝ የድንጋይ ሃውልት መጠበቅ ሳይሆን አይቀርም በዚህ ዘመን ሰው መሆን ከባድ ነው:: እኔን ጨምሮ ሰው ለራሱ እራሱ የማያውቀው ሚስጥር ነው:: በየግዜው ገላጭ ወይም ሚስጥር አጋላጭ ሁነቶች ሲያጋጥሙ ብቻ የሚገለጥ አሊያም አስመሳይ አይነት /አርቴፊሻል/ የራስ ያልሆነ ማንነት የተደፈነ ያልተገለጠ ማንነት ለእውነተኛው ግዜ ሳይታሰብ ፈንቅሎ የሚወጣ ባህሪይ፡፡

ሰው እንስሳ ነው ያለው ማን ነበር? ልክ ነው ብዬ ከዚህ ሀሳቢ ጋር ልስማማ ግን ልኩ ማሰብ ማስተዋል ክፉና ደጉን መለየቱ በመማር በእድሜና በተፈጥሮ ሚዛናዊ ጸጋዎች መጠቃቀምና በህግ አምላክና በህግ ሰው ተስማምቶና ተገዝቶ መተዳደርና መመራት መቻል ነው ሲል ሰውነቴ ይሞግተኛል ታዲያ ሰውነት ምንድነው እንስሳነት ወይስ አሳባዊነት፡- ይመለከተኛል፡፡

እንደገና ሳስብ ሰው መሆን ሚስጥር ነው ድብቅ የማይታወቅ የተለያየ ቀለማት የተዋበ በማስመሰል በተቀባ ግን የእውነት እኔ ሰው ነኝ? አዎ ነኝ ;; የሰውነት ማረጋገጫው ምንድን  ነው? ሰው መሆንስ ምን ይጠቅማል? ይሄ ጥያቄ ለምን ወደ አእምሮዬ መጣ?

እንስሳ ብሆን እኮ ይህን ጥያቄ አልጠይቅም ነብር?  አሃ ለካ ሰው ነኝ አሁን ሰው መሆኔን አረጋገጥኩ፡፡ እንደ እንስሳ እየኖሩ እንደ ሰው እያሰቡኩ ነው ብሎ ማለት በእንስሳው አለም አጉል መመጻደቅ አይሆንም ብላችሁ ነው:: በመንጋ ሀሳብ አየተመሩ፣ ዘርና ቀለም እየመረጡ፣ ጎሳ፣ ብሄር፣ ጉጥና መንደር እየለዩ እኔ ብቻ ብለው ጠርዝ ይዘው ለቆሙ የኔ ብጤዎች ሰውነኝ ብሎ ማለት ይቻል ይሆን? ይመለከተኛል፡፡

እኔጃ የሀሳቤ መነሳ ይሄ ባይሆንም ቤተሰቦቼ ሳገባ ጎሳህን፣ ዘርህን አሉ እና የኔን ሳይሆን የነሱን ተናጋሪ በሰዉኛ ሳይሆን በእንስሳኛ በከፋፈሉት የመንጋ ጎሳና ብሄር በፍቅር ሳይሆን በትዕዛዝ በክብር ሳይሆን በፍርሃት በማወቅ ሳይሆን በግዳጅ ለአበሮነት ሳይሆን ለልጅ፣ ለአቅመ ትዳር ሳይሆን ለአቅመ አዳም /ሩካቤ ስጋ/ መድረስህ ሲረጋገጥ ምነው ልጃችሁ ቆማ፣ቆም ቀረችሳ የእነገሌ ዘር የእገሌ ጎሳ የንጉስ የሀብታም ዘር አለ አለች አይደል ምናምን ወይ ሰውነት ድንቄም ሰው ይመለከተኛል፡፡

እናም እኔ እላችኋለው: —

ቆሞ መሄድህ፣ መብላት መጠጣትህ፣ ጥሩ መልበስ፣ ጥሩ መናገር ወይንም ሀብት ክብርና ዝናህ ያንተን ሰውነት በፍጹም ሊያረጋግጡልህ አይችሉምና፡፡ ይልቅ አትዘግይ!

አሁኑኑ ራስህን ፈልግ.. ዙሪያህንም አስስ..  ያንተ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ድረስላቸው። ጊዜህን ባግባቡ ተጠቀም፣ ከሚያጸጽቱህ ነገሮች ቀድመህ ለመቆጠብ ሞክር ፣ለህሊናህ እንጅ ለስሜትህም አትገዛ ላለፈ ነገር እየተጸጸትክ ቀሪ ጊዜህን አታባክን።  ከራስህ ከፍታ ይልቅ ለሰዎችና ለእምነትህ ከበሬታ ይኑርህ ፡ የወደቁትን አንሳ፣ ያዘኑትን አጽናና፣ የተራቡትንም ሽራፊ ቁራሽ አትንፈግ፣ባይኖርህም ፍቅር ስጣቸው እርሱ ከሁሉም ይበልጣልና!! ለወሬ እጅ አትስጥ በጉዞህ ሂደት ውስጥ ለሚጮሁ ዉሾች ሁሉ አትደንግጥ፣ አላማህን ለማሳካት በጽናት ጉዞህን ቀጥል ችግር መከራ ስቃይና ደስታንም አምኖ ለመቀበል ራስህን ዝግጁ አድርግ፤ ክፉን በክፉ ለመጋፈጥ ከመሞከር ይልቅ ውስጥህን በይቅርታና በመጸጸት ከተንኮል አጽዳ ፡፡

ከሰወች ጉዳትና ሞት ደስታን ወይም ሃብትን አትሻ! አትጠራጠር ያኔ! የንጹህ ልብ ህሊናና የዘላለም ደስታ ባለቤት የሃብታሞች ሁሉ ሃብታም …. የሰውም ሰው ነህ !! ስለዚህ ሰውነትን አስቀድም፡፡

ጋዜጠኛ መሐመድ ስራጅ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ስነ ልቦና

መልካምነት:- የክፋትን በር ለመዝጋት

Published

on

featured
Photo: Wikipedia

ጥቂት የመልካምነት ጠብታዎች ተጠራቅመው ትልቁን የሰብአዊነት ባህር ይሰራሉ፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ታፈራለች የሰው ልብም የመልካም ቡቃያ አውድ ናት፡፡ እኛም ከፈጣሪ የተሰጠንን ብዙ መልካም ነገሮች ውስጥ ጥቂቷን መልካምነት አጠገባችን ላሉት ሰዎች እናካፍል የሰው ልጅ መልካም ነገር ቢያደርግ ብዙ ነገሮችን ያተርፋል መልካም ስራ የክፉ ቀን ስንቅናትና፡፡

ስለዚህ ጥሩ ነገር በመስራት ለህሊናችን ሀሴትን እናቀብል፡፡ እኛም በመልካምነትና በጥሩነት ትልቅ ልንሆን ይገባል ትልቅነት የሚመጣው ከትልልቅ ሀሳቦች ነው፡፡ ሀገርም የአስተሳሰብና የመልካም ሀሳብ ውጤት ናት፡፡ ነገሮች በመልካም አስተሳሰቦችና ሀሳቦች ይደራጃሉ፡፡ ሀገርም የሚገነባው በጥሩ ሀሳብ ነውና፡፡ ሀሳብና አመለካከታችንን ወደ ጥሩና መልካም ነገር ከቀየርን የማንለውጠው ነገር የለም፡፡ አሁንም ካለንበት ችግር ለመውጣት መፍትሄው ያለው በእያንዳንዳችን መዳፍ ላይ ነው፡፡ ነገሮችን ለመቀየር እያንዳንዳችን የመፍትሄ ሀሳብ ልናዋጣ ይገባል፡፡

በመጀመሪያ የተቸገርነው ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ከዚያም ችግሮችን ለመፍታት እና ለመግታት የእኔ አስተዋፅ ምንድን ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ሁሌም ወደ መልካም አስተሳሰብ እናዘንብል፡፡ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ማተኮር አንድነትና የጠነከረ ወዳጅነት ይፈጥራልና፡፡

ሁሌም ቢሆን ለአምሮአችን መልካም መልካሙን ጥሩ ጥሩውን ልናሳስበው ይገባል፡፡ ምክንያቱም አእምሮአችን የሰጠነውን ይቀበላልና፡፡

ወደኋላ መለስ ብለን የእናት አባቶቻችንን ጥበብ እንመልከት እንዴት አድርገው ወዳጅነታቸውን እንዳጠነከሩ እንዴት መተባበርና ችግርን መሻገር እንደቻሉ እንዴት ሀገርን በነፃነት ማስቀጠል እንደቻሉ፡፡ እናስታውስ

አሁን ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ በብዙ ነገር ልንጣመር ልንዛመድ ይገባል፡፡ የበለጠ ደግሞ ልንወዳጅና ልንረዳዳ ያስፈልጋል፡፡ በከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን እናስብ እናስታውስ ለሀገራችን የተዋደቁትን ሰማህታት በህሊናችን እናመላልስ አሁን መርጠን የምንበላበት ተሽቀርቅረን የምንወጣበት ጊዜ አይደለም፡፡ አሁን የምንጨፍርበት የመዝናናት ጊዜ ላይ አይደለንም ይልቁኑ ነገሮችን በጥሞና የምንመለከትበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ብዙ ነፍስ ለኢትዮጵ ለህዝቦቿ ለእኛና ለእናንተ ተርበዋል፣ ተራቁተዋል ተሰደዋ፣ ብዙ ችግሮችን አይተዋል ክቡር የሆነውንንም ሂወታቸውንም ከፍሏል፡፡

ስለዚህ በተከፈለልን ዋጋ ነው የቆምነው፤፤ ይህን ደግሞ ከየትኛውም ጥግ ያለ ኢትዮጵዊ ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል፡፡ የሰላም እንቅልፍ የሰላም አየር መተንፈስ በሰላም ወጥቶ መግባቱ እንዲሁ በቀላሉ የመጣ አይደለም፡፡ ሰላማችን የመጣው ሀገር ወዳድ ጀግኖች በከፈሉት መሰዋትነት ነው፡፡ እነዚህን ሰማህታት ደግሞ ዋጋ ልናሳጣ አይገባም፡፡ ከቻልን የምንችለውን እናድርግ አጠገባችን ያሉትን ሰዎች እንመልከት ወገኖቻችንን እንመልከት ጦርነቱ በነበረበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ያላቸውን ችግር እንካፈላቸው፡፡ ሁሉም የአቅሙን ያድርግ፡፡ ለመልካምነት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡

ስለዚህ ለጊዜው ደስታና ጭፈራው ሆያሆዬውን ቆም አድርገን ለተቸገሩ ወገኖቻችን እንድረስላቸው እናስታውሳቸው ካልሆነ ግን “የአንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” ነውና ነገሩ “ነግ በኔ” እናስብ፡፡ ከዚህ ምድር መች እንደምንሰናበት እንኳን የማናውቅ ፍጡሮች የሰው ህመም ሊያመን ይገባል፡፡ ሁሉ ነገር በልክ ይሁን አይናችንን እና ጆሮአችንን እነዛ ለኢትዮጵያ ሲሉ ለተዋደቁ እና ለተቸገሩ ለተሰደዱ ወገኖቻችን እናውሳቸው፡፡

በተቻለን አቅም የሚጠበቅብንን እናድርግ ይህ ከሆነ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቀርብ ነው፡፡ እንተባበር እንተጋገዝ እንጎራረስ እንተሳሰብ የዚያን ጊዜ አንድነቱ ይመጣል፡፡ ልዩነታችንን አርግፈን እንጣል አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ እናትኩሩ አንድ ስንሆን ማንም አይራብም፣ ማንም አይጠማም ማንም አይራቆትም፡፡

አንድ ስንሆን ለአለም የተረፍን ህዝቦችን እንደነበርን የዓለም የታሪክ መዛግብት ምስክሮች ናቸው፡፡

በመጨረሻም አንድነታችንን እናጠናክር ለመረዳዳት እና ለማገዝ ዝግጁ እንሁን ጠንክሮ ለመስራት ወገባችንን ታጥቀን እንነሳ፤፤

ይህ ከሆነ ሁሉም ቀና ይሆናል ግድ የለም መልካምና ጥሩ ቀን ይመጣል የክፋት በሮች ሁሉ ይዘጋሉ ለቅሶና ዋይታም ይቆማሉ ስጋትና ፍርሀትም ይጠፋሉ በምትኩም ሀሴትና ደስታ ተስፋና ብልፅግና ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ይሆናል፡፡

ቤንኦን ጌታቸው።

15/05/2014 ዓ.ም

Continue Reading

በብዛት የተነበቡ