ከሁሉ በፊት አፍሪካን ለመበዝበዝ አፍሪካን ለማራቆት አፍሪካን ለመከፋፈል የውጥኑ መፍለቂያ የበርሊኑ ጉባኤ እንደሆነ ይነገራል።
የበርሊን ጉባኤ አፍሪካን ልክ እንደ ቅርጫ ስጋ በመበጣጠስና በመቆራረጥ በሚመቻቸው መጠን አፍሪካ የምትባልን አሀጉር ማሳነስና ባሪያ ድርጎ ማስቀጠል ነበር የዚህ ጉባኤ ሀሳብ አመንጪ ፖርቹጋል ብትሆንም አውሮፓውያን በሁሉም አጋጣሚ አፍሪካን አሀጉር ለመበዝበዝ ያልቋመጠበት ጊዜ አልነበረም፡፡
በአውሮፓውያን የቅርጫው ድርድር (ክፍፍል) ሲወጣ እድለቢሷ ጣልያን ከወደ ምስራቅ አፍሪካ የሆነችውን በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገችው “ኢትዮጵያ” የምትባል ሀገር ደረሳት፡፡
አንዳንድ እጣ አነሳስ ወደ መቃብር ሊያመራ እንደሚችል አላወቀችምና ጣልያን የደረሳትን ድርሻ በፈገግታ ነበር የተቀበለችው። ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብትን ነፋሻማ አየሯን የለመለመች ምድርን ለመቀራመት ባሰቡበት ሰዓት ወደ ማዕበል እሳት እየተጓዙ እንደነበር እንዴት አልተገነዘቡም ይሆን?
አይኑን በጨው አጥቦ ወደ ኢትዮጵያ እየገሰገሰ የመጣው ነጭና ወራሪው ሃይል በሀይልና በማደናገር ብርቅየዋን ሀገር ለመቆጠያጠር እቅድ ነድፎ ተንቀሳቀሰ… ከእነዚህው እቅዶች መካከል የማደናገሪያ ወይም የማምቻቻ “ውል” ማዘጋጀት ነበር፡፡
ለአድዋ ጦነት መነሳት ዋነኛ ምክንያት የሆነው የውጫሌ ውል በሚያዝያ 1881 ዓ.ም በአሁኑ አምባሰሉ ወረዳ ውጫሌ በምትባል ቦታ በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በጣሊያኑ ንጉስ አምቤርቶ መካከል ተፈረመ፡፡
የውጫሌ ውል 20 አንቀጾች ያሉት ሲሆን አንቀጽ 17 ላይ የሰፈረው ፅሁፍ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት በማጣቱ ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡
አንቀፅ 17 በአማረኛ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከአውሮፓ ነገስታት ለሚፈልጉት ጉዳይ ሁሉ በኢጣልያ መንግስት አጋዥነት መላላክ ይቻለዋል፡፡ የሚል ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም የኢትዮጵያ መንግስት ከፈቀደ ወይንም ከፈለገ በኢጣሊያ በኩል ከውጭ መንግስት ጋር ግንኙነት ማድረግ እንደሚችል የሚጠቅስ ነው፡፡
የአንቀፁ የጣልያንኛ ትርጉም ግን የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ሀገር መንግስታት ጋር የማያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት አማካኝነት ማድረግ ይገባል የሚል ነበር፡፡
ይህም የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በቀጥታ በጣልያን በኩል እንዲከናወን የሚያስገድድ ነበር፡፡
በአንቀጽ 17 አማካኝነት ጣሊያን የውሉን ሀሳብ በጣሊያንኛ በመቀየር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት በማጥፋት የጣሊያን ሞግዚት እንድትሆን ቀዳዳ ያበጀ ነው ብለው ነገስታቱ እና መኳንቱ ስለተገነዘቡ የውጫሌ ውልን እንደማይቀበሉት አሳወቁ፡፡
የኢጣሊያ መንግስትም ውሉን በተመለከተ አሻፈረኝ በሚልበት ጊዜ የውጫሌ ውል እንደፈረሰና ኢትዮጵያ ለማይቀረው ጦርነት እንድትዘጋጅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ካበረከቱ ግለሰቦች መካከል የዳግማዊ አፄ ሚኒልክ ሚስት የሆኑት እቴጌ ጣይቱ ብጡል እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል፡፡ እትጌዋ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ” ብለው ቆርጠው ተነሱ። በኢትዮጵያ የጦርነት የድል ታሪክ የሴቾች አስተዋፆ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም። በዚሁ የአድዋ ጦርነት እንኳን የሴቶች አስተዋፆ በቀላሉ የሚገለፅ አልነበረም ምክንያቱም የጦር ሜዳ ውሎ ሲነሳ መሳርያ አንግቦ ከመዋጋት ጎን ለጎን የእለት ከእለት ምግባቸውን ሳዘጋጁ የነበሩት እንስቶች ነበሩ ለአድዋ ጦርነት ለመዝመት የተሰናዳው ሀይል የምግቡን ነገር ለእናቶች እና ለእህቶች ነበር አደራ የሰጠው። ታድያ ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ በጀርባቸው ምጣድና አክንባሎ አዝለው ሊጥና ማገጆውን ሸክፈው በየመሀሉ ምግብ እያበሰሉ ሰራዊቱን የደገፋ እንስቶች ስማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ በደማቁ መፃፍ ይኖርበታል። ከዚህም በኃላ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ለመላው ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቀረቡ ከአራቱም አቅጣጫ የተመመው የኢትዮጵያ ስራዊት ወረኢሉ ከትሞ እንዲጠብቅ ከንጉሱ በኩል ትዕዛዝ ተላለፈለት። የሀገራቸውን መሪ በደስታ የተቀበሉት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ያለውን ነገር ጥሎ እምቢ ለሀገሬ ብሎ ንጉሱን ተከትሎ ጦር አንግቦ ግስጋሴውን ወደ አድዋ ተራሮች አደረገ።
የካቲት 23/1888 ዓ.ም ንጋት ላይ ሀገሬን ነፃነቴን ክብሬን አላስነካም በሚል ወገን በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእብሪት የተወጠረ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ የተቀናጀ ሰራዊት ያነገበ መካከል የተደረገ ጦርነት፡- አድዋ!
የጦርነቱ መጀመር፡- በጣልያን በኩል አሉኝ የምትላቸውን የጦር ጀነራሎችን በሶስት አቅጣጫ አስፍራ ለጦርነቱ ሰፊ ዝግጅት አደረገች። በዘመኑ የሁለቱ ሀገር ጦርነት እንዲህ በቀላሉ የሚገመት ስላልሆነ ትለቅ ሽፋን ተሰጥቶት ነበር ምክንያቱም ጣልያን በዘመኑ አሉ የሚባሉ ዘመናዊ መሳሪያ መታጠቋ፤ በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ዘመኑ ያለፈባቸው መሳሪያዎችን ቢታጠቁም የሀገሬው ንጉስ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እንዲህ በቀላሉ የማይቀመስ እና ለሀገሩ ሟች፣ መንፈስ ጠንካራ እንደነበር አሳምረው ስለሚያውቁ ለጦርነቱ ትልቅ ትኩረት ሰተውት ነበር፡፡
ጀኔራል ባራቲየሪ ሰራዊቱን በሶስት ዋና ዋና ምድብና በሌላው በኩል ደግሞ ተጠባባቂ ሀይል አመቻችቶ አሰለፈ፡፡
በመጀመሪያው ምድብ ጀኔራል አልቤርቶኔ በሁለተኛው ምድብ ጀኔራል አሪሞንዲ ሦስተኛው ምድብ ጀኔራል ዳቦርሜዳ…. ግዳጅ ተሰጣቸው ጦሩን መምራት ጀመሩ የዚህ ጦር ጠቅላይ አዛዥደግሞ ጄኔራል ኤሌኒ ሆኖ ተሾመ።
በኢትዮጵያ በኩል ጦሩን በዋናነት ይመሩ የነበሩት ንጉሰ ነገስት ዳግሚ አፄ ሚኑሊክ ነበሩ ነገር ግን የጦር አበጋዞቹ “ንግስት ጣይቱ፣ ፊት አውራሩ ገበየሁ መኮንን፣ ራስ መንገሻ ዮሃንስ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ ሃጎስ፣ ንጉስ ተክለሃይማኖት፣ ራስ ወሌ፣ ራስ ሚካኤል ፣ ልዑል እራስ መኮንን ፣ዋግሹም ንግጉል፣ እራስ መንገሻ አቲኮም እነዚህ ዋና ዋናዎቹ የጦር መሪዎች ነበሩ፡፡
በሁለቱ ጦር መካከል ፈፅሞ የማይመጣጠን የጦር መሳሪያ ነበራቸው፡፡
ኢጣልያን በጣም የተሻለ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀች ሲሆን ኢትዮጵያ ግን በዘመናዊነቱ እጅጉን ያነሰ ነበር፡፡ ሁለቱም ተፋላሚዎች ወደ ጦርነት ለመግባት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡
በአንድ በኩል ክብሬን ሀገሬን ነፃነቴን ህዝቤን አላስነካም አላስደፍርም በሚል ነፃነትን የሚያስቀጠል እራእይ የሰነቀ ጦር… በሌላ በኩል ደግሞ በእብሪት የተወጠረ የሰው መሬት ሲበላ የቋመጠ ታሪክ ሊያበላሽ ሊገዛ ሊገድል የመጣ ወራሪ ጦር…
ከሁሉም የላቀው የአድዋ ጦርነት ውጊያው የተጀመረው የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከጠዋቱ 11 ሰዓት ከ 32 ደቂቃ ላይ የጀኔራል አልቤርቶኔ ክፍለ ጦር በፊት አውራሪ ገበየሁ፣ በዋግሹም ጓንዱል፣ በራስ ሚካኤልና በራስ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ጦርነቱ ተከፈተ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በባዶ እግራቸው ያን የአደዋ ተራራ ሲወጡት ለተመለከተ የእውነት ወደ ጦርነት ሳይሆን የሚጓዙት ደስታ ሰንቀው ለእምዬ ኢትዮጵያ ምንስ ቢሰጥ የሚለውን ሀሳብ በእጅጉ አሳይተዋል። ኢትዮጵያ በየዘመኗ ለህልውናዋ ለመጣ ለነፍሱ የማይሳሳ የማይራራ ጀግና መፍጠል የምትችል ብርቅዬ ሀገር ናት። በአለም ላይ ተጨቁነው ለቆዩ ለአለም ህዝብ በሙሉ ነፃነትን ያስተዋወቀች የአፍሪቃ ፈርጥ የነፃነት ብሌን ናት።
የንጉሰ ነገስቱ የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ሰራዊት የመሀል ጦር አዛዥ ፊት አውራሪ ገበየሁ በዚህ ከጣልያኖች ጋር በተደረገ ጦነት የተመሰከረለት ጀግና ነበር ።
ጎራዴውን መዝዞ በዋናው የትግል አውድማ ላይ ወኔና ጀግንነቱ ከፊቱ ላይ የማይጠፋው የሀገሬ አርበኛው ገበየሁ የጣልያን ወታደሮችን እንደ ቅጠል ያረግፋቸው ተያያዘው፡፡ ሀገራቸው ስትነካ የማይወዱ ጀግኖች በፍልሚያው ሜዳ ላይ ትልቅ ተጋድሎ አደረጉ፡፡ ሞት ለሀገር ሲሆን ክብር ነውና ፊት አውራሪ ገበየሁ ሺዎችን ጥሎ ለአንዲት ሀገሩ ነፍሱን ገበረ።
የኢትዮጵያ ሰራዊት ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን ወራሪ የጣሊያን ጦር በያለበት እያሳደደ ይረፈርፈው ጀመር፡፡
ይህ ነገር ለጣልያኖች ትልቅ መደናገጥን ፈጥሮ ነበር፡፡ የጣሊን ወታደሮች በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ቢፋለሙም የሀገሬ ጀግኖች በጨበጣ ውጊያ ወራሪውን ሀይል መቆሚያ መቀመጫ አሳጧቸው፡፡ እየተከታተሉ መድረሻ አሳጧቸው፡፡ ውሃ ጥም ያልበበገረው እርሃብ ያላሰነፈው ነፃነቱ ስንቁ የሆነው አርበኛው ተዋጊው የኢትዮጵያ ጦር የጦር ሜዳውን በሬሳ ሞላው፤፤ በዚህ ሁሉ መሃል ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ከተራው ወታደር እኩል እየተዋጉ ትዕዛዝ እየሰጡ አይበገሬነታቸውን አስመሰከሩ፡፡
ቆራጡ መሪ እምዬ ሚኒሊክ የጥቁር ህዝቦች ፈርጥ ለአፍሪካ ነፃነት ፋና ወጊ አንፀባራቂ የአበሻ ምድር ጀግና በጦር ሜዳ ውስጥ ሆኖ ጣልያኖችን እየደቆሰ መድረሻ አሳጣቸው፡፡
በዚህ መሃል በመጀመሪያው ምድብ ላይ የተሰለፈው የጣልያን የጦር መሪ ጀኔራል አልቤርቶኔ የተቀመጠበት በቅሎ በኢትዮጵያ ሀይሎች ስለተመታች ከበቅሎ ላይ ወደ መሬት ተዘረረ ኢትዮጵያውያን ትንታጎች ተወርውረው ጀኔራ አልቤርትኔን ማረኩት ከዚያም የጣልያን ወታደሮች ተደናግጠው ፈረጠጡ አልነካም ያለው የሀገሬ ሰራዊት ከኋላ እየተከተለ በጦርና በአንካሴ ያራሩጠው ጀመር፡፡
በተጨማሪም ጀኔራል አርሞንዲ በመሀል ተመቶ መሬት ላይ ተዘረረ የጣልያ ወታደሮች የበለጠ ተደናገጡ፡፡
ጀኔራል ዳቦረሜዳም በሽሽት ላይ እያለ በኢትዮጲያውያን ትንታጎች ተመቶ መሞቱን የተመለከተው የኢትዮጵ ጦር ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡ በጦርነቱ መሀል ኢትዮጲያውያንን ጀግኖት የተመለከት የሰሩት ጀብጁ ለሀገራቸው የከፈሉት ዋጋ በምን አንደበት ይገለፅ ይሆን ምን አይነት ቃላት ይገለፀው ይሆን እናንት የኢትዮጲያውያን ብቻ ሳይሆን ለአለም ጥቁር ህዝቦች እንደ ብርሃን ስታበሩ ትኖራችሁ ታሪካችሁም ለዘላለም ይወሳል አክብሮትና ውዳሴ ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለእናንተ ይሁን። ጦርነቱ እየተገባደደ ሲመጣ ንጉሰ ነገስቱ ደግነት አያልቅባቸውምና የጠላት ጦር በፍቃዳቸው እጃቸውን እንዲሰጡና እንዳይገደሉ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡
የጀኔራል ባራቲየር ሰራዊት አደዋ ላይ ተሽመድምደው መሸነፉቸውን በመላው አውሮፓውያን ቀዳሚ ዘገባቸው አደረጉት፡፡ ለመላው አፍሪካውያንም መነቃቃትን ፈጠረ፡፡ በአለም ላይ አዲስ ክስተት ተከሰተ ጥቁሮች በጦር ሜዳ ተሰልፈው በራሳቸው ወግና ባህል ወኔና ጀግንነት ነጮችን ማሸነፍ እንደማችል የብስራት ደውል ተደወለ፡፡
አይቻልምን ወደ ይቻላል የቀየሩ ለአለም አዲስ ክስተትን ያስተዋወቁ ነፍሳቸውን የገበሩ አጥንታቸውን የከሰከሱ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ውለታቸው ምን ይሆን ብድራታቸውስ እንዴት ይከፈል ይሆን፡፡
የአድዋ ድል የአፍሪካ ጦር የአውሮፓውያንን ጦር የደመሰሰበት ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሃይሎች ከነጭ አውሮፓውያን ኃይሎች ጋር በመፋለም ታሪካዊ የበላይነትን ያስመዘገቡበት አንፀባራዊ፣ አስደናቂ ድል ነው፡፡
አድዋ ለሰለጠነችው ጣልያን ታላቅ ውርደትና ሞት፣ ለነጭ አውሮፓውያን በሙሉ ደግሞ ሃፍረትና ስብራት ሲሆን ለኢትዮጵያን እና ለመላው ጥቁር ህዝቦች ደግሞ ደማቅ የድል ድል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
የኢትዮጵያ የአድዋ ድል አለምን የታሪክ አካሄድ የለወጠ ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የበላይነት ያፈረሰ ለነጭ ገዢዎች መራር የማይዋጥ የሆነበት ለጥቁር ህዝቦች ግን ታላቅ ትንሳኤና የማንነት ትግል የተረጋገጠበት ሆኖ አልፏል፡፡
አድዋ የማይሰረዝ የማይጠፋ የማይቀየር እስከ ለአለም የሚኖር አልፋና ኦሜጋ ነው፡፡ አድዋ የአካልና የመንፈስ ጥንካሬ የፅናት ተምሳሌት ነው፡፡ እኛም በደማቸው ጠብቀው ያሰፋትን ምድር በአስተሳሰባችን አናጥበው አንድ ለመሆን የተዋደቁ እናት አባቶቻችን አጥንትና ደማቸው አደራ ይሁነን ለሀገሩ ክብር ሲል ደረቱን ለባሩድ የሰጠው ወገኔ መንፈሱ አይውቀሰን ያንን ጊዜ እናስታውስ ለአንዲት ኢትዮጵያ እንጓዝ በብሔር አስተሳሰብ አንነስ። እኛ የማን ልጆች እንደሆንን እናሰላስል የአባቶቻችንን የሞራል ልዕልና እንውረስ። ራሳችንን እናክብር ሀገራችንንም በተግባር እንጥቀም።
አድዋ በታሪክ ፈለግ ውርሳችን ይበልጥ የምንተሳሰብበት ይሁን የአንድ ስልጣኔ ወራሽ መሆናችንን የምናውቅበት የአንዲት ኢትዮጵያ ልጆች መሆናችንን የምናስገነዝብበት መሆኑን እንረዳ ኢትዮጵያዊነት ባለብዙ ቀለም አውታር ህብር መሆኑን የምናስገነዝብበትና የሚያስተቃቅፈን የታሪክ ድልድያችን ይሁን።
የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማህተም የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀንዲል ነው፡፡
አድዋ ለመላው አለም ተፈጥሮአዊና ሰብአዊ ክብር የታደሰበት በእውነትና በፍትህ ነፃነት የታወጀበት እስከ ዘላለም የሚኖር አኩሪ ታሪክ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በፍቅር እንጂ በጉልበት በእብሪት የማትንበረከክ ለወራሪዋ ህመም ለጠላቶቿ መራሪ ሃሞት መሆኗን ያስመሰከረችበት ለአለም የማይቻለውን በመቻል ያሳየችበት አንፀባራቂ ድላችን አደዋ፡፡
አድዋ ትከሻው በጎጠኝነት ትምክህት ያልጎበጠ ጀርባው በጎጥ ያልተጋጠ ጀግና ትውልድ የሰራው አይተኬ ታሪካችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ምድር ነፃነት ያላቸው ህዝቦች መኖሪያ ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ ተመርምሮ የማይደረስበት ልክ እንደ እምነት የጠለቀ ነው፡፡
በቤንኦን ጌታቸው
21/06/2014 ዓ.ም