በጦርነት ሀሩር መገረፍ ከጀመረች 10 ዓመታት ያስቆጠረችው ሶሪያ ከዛሬ ነገ ይሻላታል ቢባልም አሁንም ያለ ለውጥ መጎዟን ቀጥላለች፡፡ ይባስ ብሎም በተለያዩ ጊዜያት ከእሥራኤል ወደ ሶሪያ የሚወነጨፉ ሮኬቶችና የድሮን ጥቃቶች ነዋሪዎቿን እንቅልፍ ከነሳ ዋል አደር ብሏል፡፡
ታዲያ እሥራኤል አሁንም ከሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ በስተ-ደቡብ የምትገኘዋን ዛኪህ ከተማን መደብደቧ ተሰምቷል፡፡ አህሉል ባያት የዜና ምንጭ የእሥራኤል ወታደራዊ ኃይሎች ተምዘግዛጊ ሮኬቶችን በማስወንጨፍ የሶሪያን ደቡብባዊ ክፍል ከተማ የሆነችውን ዛኪህን መደብደባቸውን አስነብቧል፡፡ የዜና ምንጩ ከሶሪያ ባለስልጣናት አገኘሁት ባለው መጃ መሠረት ወደ ከተማዋ ሮኬቶች ቢወነጨፍም በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ዩሮ ኒውስ በበኩሉ ከደማስቆ ደብቡ ምዕራብ ገጠራማ ከተማ በምትገኘው ከካን አል ሺህ ከተማ ውጭ ለሰዓታት የቆየ ተከታታይ ፍንዳታ መስማቱን ገልጿል፡፡
የሶሪያ ወታደራዊ ባለስልጣናት በበኩላቸው እንደገለፁት ሮኬቶቹ እሥራኤል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ1967 ጀምሮ ተቆጣጥራ ከያዘችው የሶሪያ ጎላን ኮረብታማ ቦታዎች የተተኮሱ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
የጦር ባለስልጣናቱ አያይዘውም ሲተኮሱ የነበሩ ሮኬቶች አደጋ እዳያደርሱ አድርገን አምክነናቸዋል ማለታቸው ተገልጿል፡፡ ታዲያ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ በበኩላቸው እስራኤል በሶሪያ ላይ የምታደርሰውን ተደጋጋሚ ጥቃት ልታቆም ይገባል ፤ ሳትውል ሳታድርም እጇን ከሶሪያ ላይ ታንሳ ማለታቸው ነው የተገለፀው፡፡ ቃል አቀባዩ አክለውም ይህ ጥቃት በእንዲህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ የሶሪያ ዜጎች ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ የሚከት ስለሆነ ከወዲሁ ሊተሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡
የሶሪያ የሰብዓዊ መብቶች ታዛቢ ራሚ አብደል ራህማን ለኤኤ.ፍ.ፒ እንደተናገሩት ጥቃቱ ያነጣጠረው የሶሪያ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ አያይዘውም እንደገለፁት በሰው ላይ የደረሰው ጥቃት መኖሩን እያጣራን ነው ማለታቸው ተገልጿል፡፡
ሶሪያ በእርስ በርስ ጦርነት መናጥ ከጀመረችበት የፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ እሥራኤል በመቶዎች የሚቆጠሩ የሮኬት ጥቃቶችና የአውሮኘላን ጥቃቶችን ማድረሷ ቢነገም የእሥራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናት ግን ድርጊቱን አድርገነዋል ሲሉ እስካሁን ተናግረው አለማመናቸው ይነገራል፡፡
ታዲያ የእርስ በርስ ጦርነት ብሎም ከየአቅጣጫው የሚሰነዘሩ ጥቃቶች የበሽር አል አሳድን መንግሥት ባያስደነግጠውም የሀገሪቱን ዜጎች ግን የዛፍ ላይ እንቅልፍ መተኛት ከጀመሩ ድፍን 10 ዓመታትን ተሻግረዋል፡፡ ይባስ ብሎ ችግሩን የመረረ እና የከፋ የሚያደርገው በቀየኑ በገበያ ተቋማትና በየአውራ ጎዳናዎች የሚደርሱት የሽብር ጥቃቶች መበራከታቸው የዜጎችን ህይወት ከድጡ ወደ ማጡ እንዳደረገወ ይገለፃል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው እሥራኤል ተኮሰችው ከተባለው የሮኬት አረር ለማምለጥ ሲሸሹ የነበሩ ሶሪያውያን በመኪና ላይ በተጠመደ ፈንጂ ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ህይወታቸው መቀጠፉ አንዱ ማሳያ ነው፡፡
የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ታዲያ ተጨማሪ የደረሰውን የፈንጂ ጥቃት እንደገለፁት የጥቃቱ አድራሽ በሀገሪቱ ሽምቆ የሚንቀሳቀሰው የአይ.ኤስ.አይ.ኤስ አሸባሪ ቡድን ሊሆን ይችላል ሲሉ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት በፈረንጆቹ 2021 መጨረሻ ባወጣው ሪፖርትም እንዳመለከተው በሶሪያ እየደረሰ ያለው አሰቃቂ የጦር ዘመቻ አለም አቀፍ የጦር ወንጀል ነው ሲል ያለውን ችግር ግዝፈት አስነብቧል፡፡ ይሁን እንጂ በየጊዜው አዳዲስ ጉዳዮችን በሶሪያ ላይ ቢያስነብቡም በሀገሪቱ የነዳጅ የምግብ ብሎም የመድኃኒት እጥረት ዜጎችን የከፋ መቀመቅ እየከተታቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጠናሁት ብሎ ባወጣው መረጃ መሠረትም እስከ ፈረንጆቹ 2021 መገባደጃ ባስጠናው ጥናት አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሶሪያውያን ቁጥር 21 በመቶ ጨምሯል ያለ ሲሆን በድምሩ 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሰዎች ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን አትቷል፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት ከሰብዓዊ መብት አጥኚ ድርጅቶች አገኘሁት ባለው መረጃም በሀገረ ሶሪያ በአይ.ኤስ.አይ.ኤስ በሚመራ የሽብር ቡድን አማካኝነት 60 ሺ የሚደርሱ ንፁሃን ዜጎች በአስከፊ ማጎሪያዎች የመታሰራቸውን የገለፀ ሲሆን ችግሩን ግዘፍ የነሳ የሚያደርገው ደግሞ በርካታ ሴቶችና ህፃናት የገፈቱ ቀማሽ መሆናቸው እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለም የሀገሪቱ ነዋሪዎች ካለው ጦርነት ጎን ለጎን የከፋ ጉዳት እያደረሰባቸው የሚገኘው ከቀን ወደ ቀን እየጋሸበ የመጣው የኑሮ ውድነት እንደሆነ በየጊዜው ሲነገር ይደመጣል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ወርልድ ቪዥን አጠናሁት ባለው የሀገሪቱ የኑሮ ውድነት ሁኔታ አሁን ላይ በሶሪያ ጦርነቱ ባስከተለው ችግር 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ዶላር ኪሣራ በመድረሱ የኑሮ ውድነቱን እጅጉን የከፋ አድርጎታል ሲል በጥናቱ አመላክቷል፡፡
በተደጋጋሚ ሀገሪቱን በተመለከተ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ፅንፈ የረገጡ የምዕራቡ አለም ሽኩቻዎችን የበላይነት ማሳያ እና ማስተግበሪያ ሶሪያ መሆኗ ለዚህ መቀመቅ እንዳደረጋት ይገልፃል፡፡ ብሎም በሀገሪቱ የመሸጉ የበሽር አላሳድ ደጋፊዎችን ጨምሮ እንደ አይ.ኤስ መሰል እጀ ረጅም የአሸባሪ ቡድኖች የሶሪያ ህልውና ከድጡ ወደ ማጡ እንደከተቱት የማያባራው ሰቆቃ ማሳያ ነው፡፡
ትንታኔ ዘገባውን ስናዘጋጅ አልሀሉል ባያትን፣ አልጀዚራና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድህረ-ገፅን ተመልክተናል፡፡
በዮሐንስ አበበ