የዓድዋ ድል የዓለምን የኃይል አሰላለፍ ይዘት የገለበጠ፤ ከዛ ቀደም የነበረውን የምድራችን የታሪክ መልክ የቀየረ፤ “ነጭ ነጭ” ብቻ የሚልን ትርክት የቀለበሰ፤ አዲስ መንገድን የቀደደና ይደለደላሉ፤ ስለመሆኑ የሚናገሩት ብዙዎች ናቸው። የድሉን ገናንነት የሚመሰክሩት ደግሞ በጦርነቱ የተሸነፈችውን የጣሊያን ጸሐፍት ጨምሩ የሌሎችም የአውሮፓና የአሜሪካ የታሪክ አጥኚዎች ናቸው። በዓድዋ ድል ዙሪያ እሰከ 18 የሚደርሱ የታሪክ ድርሳናትን በግለሰብ ደረጃ ብቻ በአድናቆት የጻፉ የእንግሊዝ፣ የጀርመንና የጣሊያን ተመራማሪዎች መኖራቸውንም ዓለም በግርምት ታዝቧል።
ዓድዋ የጥቁሮች የነጻነት ደወል በተለዬ ሲሆን፣ በጥቅሉ ደግሞ የዓለም ጭቁኖች ሁሉ የተነቃቁበት የአርነት ጥሪ ነው። ሰው ከሰው መካከል የተበላለጠ የበላይና የበታች ተብሎ በሸፍጥ የተሰበከውን ልማድ ገለባብጦ የጻፈ ዐዲስ በደም የተጌጠ ኅያው መዝገብ ነው።
ከዘመን ዘመናት የተሻገረው የነጮች በዝባዥነት በአሐጉረ አፍሪካ እንዲያከትምም መነሻ ነጥብ ሆኖ የተነደፈ ደማቅ መስመር ነው የሚሉም አያሌዎች ናቸው። ዓድዋ እኩልነት የተባለ ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተመዘገበበት የሥነ ሰብ ቅዱስ መጽሐፍ ነው ያሉትም የመላው የፕላኔቷ ልሳናት ናቸው።
በ1884ቱ የበርሊን ስብሰባ አፍሪካን እንዴት በሰላም (የነጭ ደም ሳይፈስስ) እንቀራመታት ያሉት አውሮፓውያን መላ አሐጉሪቱን ሲወሯት በራሷ ኃይል ብቻ ወረራውን የቀለበሰችው ኢትዮጵያ፣ በኋለኛው ዘመን ለመጣው የአፍሪካ ነጻነት የማይሻረውን ንቅናቄ አሲዛበታለች በዓድዋ። ፓን አፍሪካኒዝምን በጥቁር አብዮተኛ ልቦች ላይ አትማበታለች ኢትዮጵያ።
የታሪክ ተመራማሪና መምሕሩ አቶ በላይ ስጦታው በነጮች ሳይቀር የተመሰከረው በምድር ከተካሔዱ ጦርነትና ድሎች ሁሉ ዓድዋ ቀዳሚው መሆኑ የተረጋገጠ መሆኑን ያነሳሉ።
በአንድ ወቅት ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ ከዛም አልፎ እስከ ላቲንና ኤዥያ ከተደረጉት ጦርነቶች ትልቁ ጦርነት ድል የትኛው ነው ትልቁ ሲል ቢቢሲ ባዘጋጄው የጥያቄና መልስ ውድድር “ዓድዋ” ብሎ የመለሰው ጋናዊ ወጣት አሸናፊ የሆነበትን ሁነት ደግሞ እንደ ማስረጃ ያቀርቡታል አቶ በላይ።
የዓድዋ ድል ትልቅ የሃገር ቅርስና የአንድነት አርማ መሆኑን የሚናገሩት ሌላው የታሪክ ሙሕር አቶ ደረጄ ተክሌ ዓድዋን በሚገባው ደረጃ ማወቅና ማክበር ይገባል ብለዋል።
አያይዘውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓድዋን ብሔራዊ በዓልነትና የአንድነት ድልነትን የሚሸረሽሩ ነገሮች መታየታቸውን ጠቅሰዋል።
ስለሆነም በትምሕርት ቤቶች፣ በባህልና ታሪክ ተቋማት፣ በመገናኛ ብዙኃንና በሌሎችም መሰል መንገዶች ዓድዋን በሚገባ ማስተማርና ማስተዋዎቅ ይገባል ባይም ናቸው።
ስለ ዓድዋ ድል ሲታሰብ: የክርስቲያን ሙስሊሙ፣ የደገኛ የቆለኛው፣ የወጣት የአዛውንቱ ባጠቃላይ የመላው ኢትዮጵያዊ መሆኑን ማሰብ ይገባናል የሚሉን ደግሞ ሌላኛው የታሪክ ጥናት ተመራማሪ ፕ/ር አሕመድ ዘካሪያ ናቸው።
ፕ/ሩ ዓድዋ በአንድነት ስንቆም የማንችለው ፈተና እንደሌለ የምንረዳበት መሆኑንም ነው የሚያብራሩት።
የታሪክ መምህሩ አቶ በላይ ስጦታው በነጮች ተንኮልና ሴራ በትውልዶች መካከል የተነዛውን በማንነትና እምነት መለያዬት የሚፈውሰው መድሐኒት ዓድዋ መሆኑን አስረድተዋል። ዘመናት ለማይሽሩት የነጮች የመከፋፈል አዝማሚያም መበገር እንደማይገባ ነው የሚገልጹት ሙሕሩ።
ከሃገር ፍቅርና ታሪክን ከማወቅ አንጻር የአሁኑ ትውልድ ክፍተት አለበት ይባላልና ፤ አባባሉ በዘርፉ ሙሕራን አይን ሲታይ ምን ያህል ትክክል ነው ያልናቸው አቶ ደረጀ ተክሌ፣ ትውልዱ ላይ ሳይሆን ችግሩ ያለው ሊኂቃኑ ጋር ነው ብለዋል።
በመሆኑም ሊኂቃሉ ከጎሳ የፖለቲካ አተያይ ተላቀው እውነተኛውን ኢትዮጵያውነት ማስተማር ይገባቸዋል ብለዋል። አንድነት የማይበጠስ ኃይል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ሁሉም ትውልድ የራሱ ዓድማ ያለበት መሆኑን የሚያነሱት ሙሕራኑ በዚህ ዘመን ለሚጠበቀው የሃገር ጥሪም እንደ አባቶቻችን አመርቂ መልስ እንደሚጠበቅብን አንስተዋል።
በያለው አዛናው