በበጄት ዓመቱ ለ2.7 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል :- የሥራና ክሕሎት ሚኒስቴር
በበጄት ዓመቱ ለ2.7 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክሕሎት ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በየ ዓመቱ ለ2 ሚሊዮን ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ተስቦ በ2014 ዓ.ም የተቋቋመ ዐዲስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ነው።
ሁለተኛው የሥራ ጉባዔ “ ዘላቂ ሥራ ለብሩህ ነገ ” በሚል መሪ ቃል ከነሐሴ 09 እሰከ 10 2014 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ተካሒዷል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ጉባዔውን በይፋ ሲክፈቱ እንደተናገሩት ሁለተኛው የሥራ ጉባዔ በሥራ ዕድል ፈጠራ ፣ በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ እና የሥራ ደህንነት ዘርፎች ጠቃሚ የሆኑ የፖሊሲ ግብአቶች የሚገኝበት ነው፡፡
በሃገራችን ከፍተኛ የሆነ ሥራ አጥነት መኖሩ፣ የፈጠራና ክሕሎት ልማዶች አነስተኛ መሆናቸው እና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ሠፊ ንቅናቄ መፍጠር ማስፈለጉ ደግሞ ለመሥሪያ ቤቱ በሚኒስቴር ደረጃ መቋቋም ሌላ ገፊ ምክኒያት ነው።
የሥራና ክሕሎት ሚንስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በሃገራችን ሠፋፊ የሥራ ዕድሎችን ካልፈጠርን የሥራ አጡ በቁጥር በየ አመቱ ባያሌው የሚጨምር መሆንኑ አውቀናል ብለዋል። ስለሆነም ከታቀደው በላይ መሥራት ያሻልም ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ በርከት ያሉ ጊዜአዊ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል ያሉት ሚኒስቴሯ በቋሚነት ለ2.7 ሚሊዮን ዜጎች ሥራ መስጠት ተችሏል ባይ ናቸው። ስኬቱ የሚያኩራራና አይደለም ፤ ከዚህ በላይ መሥራት ግድ ይለናል የሚለውንም ጨምረዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራውን የግብርናው መሥክ በስፋት እንዲሸፍን የመንግስት ፖሊሲ ነው ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚህም መሠሰት 46 በመቶውን እንዲሸፍን ታስቧል ብለዋል። ነገር ግን በዓመቱ 26 በመቶውን ብቻ እንደሸፈነ ጠቅሰው ለዚህ አነስተኛ ስኬት መገኜት ማነቆ የሆኑት የኢንዱስትሪ ትስስር አለመኖር እና የግብርና ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ መሸጥን አለመለማመዳችን ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ሥራ ሁለንተናዊ ዕይታ እና ምልከታ ይፈልጋል ያሉት ሚኒስቴሯ ሙፈሪሃት ተበታትነው የነበሩ ሥራን ማዕከል ያደረጉ ተቋማትን ወደ አንድ በመሰብሰብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከተቋቋመ በኋላ ዘርፎቹ ያሉባቸውን ማነቆዎች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምሰሶዎች በሆኑት የሥልጠና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የኢንዱስትሪ ሰላም ወይም የሥራ ቦታ ደህንነት ዘርፎች የገበያውን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ሰፊ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን በመግለፅ ከተለያዩ አጋር አካላት እና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር የተፈጠሩትን የቅንጅት ሥራዎች ከጅምር እንቅስቃሴዎች መካከል ሚኒስትር ሙፈሪሃት በቀዳሚነት ጠቀሰዋቸዋል፡፡
በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በነበረው ጦርነትና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ የማያቋርጡ ግጭትና ውድመቶች በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩንም ተናግረዋል።
ተቋምን እያቋቋመ በጦርነት የወደሙ ኢንተርፕራይዞችን እና ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመደገፍ ባለፉት ወራት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን የተናገሩት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ሁለተኛው የሥራ ጉባዔ በማይቋረጠው የለውጥ ሂደት ውስጥ ለሚተገበሩ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች የፖሊሲ ሃሳቦችን አንጥሮ እንደሚያወጣ እንጠብቃለን ብለዋል ፡፡
ሁለተኛው የሥራ ጉባዔ ዘርፉን የተመለከቱ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ደምቦችና መመሪያዎች እንዲሁም አሰራሮችን ለመፈተሽ የሚያግዙ ሀሳቦች የሚሰባሰቡበት እና የዘርፉ ባለሙያዎች የሚበረታቱበት ነው ያሉት ደግሞ
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ንጉሡ ጥላሁን ናቸው።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የሥራ ጉባዔ ተሳታፊዎች ልምድ የሚለዋወጡበት ፣ ከሚቀርቡ ችግር ፈቺ ጥናቶች የፖሊሲ ግብአቶች የሚገኝበት፣ የዲጂታሉን ዓለም ለሥራ እና ስልጠና ለመጠቀም የሚያስችል ውይይት የሚካሄድበት መሆኑንም አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡
ከስልጠና እና ከፋይናንስ አኳያ በተሻለ ሁኔታ ኢንተርፕራይዞችን የደገፉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ዕውቅና የሚያገኙበት ሁለተኛው የሥራ ጉባዔ ውጤታማ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን መነሻ በማድረግ ንቁ እና ለሥራ የተዘጋጀ ወጣት በመፍጠር ሂደት በተለይም ለሚያጋጥሙ ችግሮች መፍትሔ የማበጀት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንደሚኖሩት ተስፋ አለኝም ብለዋል፡፡
ለጉባዔው ከቀረቡ 15 ጥናታዊ ፅሁፎች መካከል በባለሙያ የተመረጡት 4ቱ ቀርበው ውይይት የሚደረግባቸው ሲሆን በሠራተኛ አቅርቦት፣ ፍላጎት እና በሥራ ሥምሪት ትስስር፣አፈፃፀም፣ ተግዳሮች እና መፍትሄዎች ላይ የሚመክር ፓናል ውይይትም ተካሒዷል፡፡
በዲጅታል የሥራ ፈጠራ ዘርፍ በተሰማሩ አካላት መካከል በሀገሪቱ የዲጂታል ኢንተርፕርነርሽፕ ሥነ-ምህዳር ግንባታ ረገድ የመንግስትና የግሉን ዘርፍ ሚና እና ድርሻ እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች መፍትሄዎቻቸው ላይ በዘርፉ ምሁራን እና ባለሙያዎች የሚደረገው ውይይትም የጉባዔው አካል መሆኑን አቶ ንጉሡ ገልፀዋል፡፡
ከተለዩት 10 የንግድ ሥራ ሃሳብ ባለቤቶች በዚህ ጉባዔ 5 ዳኞች በተገኙበት የንግድ ሥራ ሃሳባቸው ቀርቦ ከ10ሩ ውስጥ ምርጥ 3 ተለይተው ለንግድ ሥራቸው መጀመሪያ የሚሆን የገንዘብ ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡
የተሻለ አፈፃፀም ያስመዘገቡ 60 የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች እንዲሁም 60 ባለሙያዎች፣ 280 ወደ ታዳጊ የተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች፣ 102 የላቁ ሞዴል ኢንተርፕራይዞች፣ 6 ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ያደረጉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ተቋማት፣ 3 ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ያደረጉ የአነስተኛ ፋይናንስ ተቋማት ፣ 3 የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው የግብርና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ዕውቅና እና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡
በሃገራችን በየ ዓመቱ ለመፍጠር የታለመው ዐዲስ የሥራ ዕድል ግቡን እንዲመታ ከሁሉም የመንግስትና የግሉ ተቋማትና ድርጅቶች ብዙ እንደሚጠበቅም ሚንስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል ተናግረዋል።
በ ያለው አዛናው