የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው — በሀገሪቱ እየተፈፀሙ ያሉ በደሎች ከኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባርና ስነ-ልቦና የወጡ ናቸዉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዜጎች ላይ ብሔር ተኮር ጥቃቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለፁ ይታወሳል፡፡
የሀገሪቱ ዜጎች ወደተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ የመስራት መብት ቢኖራቸውም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ የሰብዓዊ ጥሰቶች እየተፈፀመባቸው ይገኛል፡፡
ዜጎች ምንም በማያውቁት ለሞት፣ ለስደትና ለእንግልት እየተዳረጉም ይገኛሉ፡፡
በዚህም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች ሀብትና ንብረት ካፈሩባቸው ክልሎች ተፈናቅለው ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ይታወቃል፡፡
ከጣቢያችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ አያሌው በሀገሪቱ እየተፈፀሙ ያሉ በደሎች በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባርና ስነ-ልቦና የወጡና በሀገሪቷ ታሪክ ተሰምቶ የማይታወቅ በደል እየተፈፀመ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
የታሪክ ተመራማሪና ፖለቲከኛ ዶ/ር ሙሉ ነጋ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን ዜጋ በመገፋፋት ማመን እንደሌለበት ገልፀው የአንዱ ጥቃት የሁሉም ጥቃት መሆን አለበትና የአንድ ልማት የሁሉም ልማት ተደርጎ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሊወሰድ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ዶ/ር ሙሉ ነጋ አክለውም ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች የሚንቀሳቀሱት በህገ መንግሥቱ ህግና ስርዓት ስለሆነ ማንኛውም አካል ለህገ መንግሥቱ ተረዢ እስከሆነ ድረስ መንግሥት በዜጎች ላይ እየተፈፀመና እየተደረገ ያለውን በደል ትኩረት ሰጥቶ ዜጎች በየትኛውም አካባቢ ተዘዋውረው የመስራት መብታቸውን ሊያስጠብቅ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡
በቀድሞ የህውሓት ስርዓት አንዱ የአንዱን ብሔር ጨቋኝና በዳይ ተደርጎ ሲነገር እንደነበር የተናገሩት የእናት ፓርቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈስላሴ ለዚህም በቅርቡ ለሚደረገው ሀገራዊ ምክክር ሁሉም አካል ለመወቃቀስና ለመወነጃጀል ሳይሆን የቀድሞ ጠባሳችንን በመተው ሀገራችንን አንድ በሚያደርጉና ለሀገራችን ዜጎች ዘላቂ ሰላምን ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ በመወያየት የሀገራችንን ሰላም ማስጠበቅ አለብን ብለዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት በመላው ሀገሪቱ በተከሰቱ የብሔርና የእምነት ተኮር ግጭቶች ጋር በተያያዘ ከ10 ሺ በላይ ሰዎች ክስ እንደተመሰረተባቸው ነገር ግን የፍትህ ሂደቱ የተሳካ እንዳይሆን የፖለቲካ መዋቅሩ እክል መፍጠሩን የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥም ክስ የተመሠረተባቸው ወንጀለኞች በመደበኛው የወንጀል የፍትሕ አካላት ክስ ተመስርቶ ወንጀለኞችን ለማጣራትና ክስ መስርቶ ለመሄድ የተደረገው ሙከራ ፍትሕን ለማረጋገጥ አስችሏል ተብሎ በበቂ ሁኔታ ለመግለፅ አያስደፍርም ሲሉ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወቃል፡፡
ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ የተቋሙን የ2014 ዓ.ም የ6ኛ ወር የዕቅድ አፈፃፀሙን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት መንግሥት ከሳምንታት በፊት ጉዳቸው በህግ እየታየ የነበሩ የሕውሓትና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ክሳቸው ተቋርጦ ከእሥር መፈታታቸው ከፓርላማ አባላት በርካታ ጥያቄ ተነስቶበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በያሬድ እንዳሻው