የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየአመቱ ላለፉት 13 ዓመታት በ 10.8 በመቶ እያደገ እና በአከባቢዉ ካሉት ከፍተኛ እደገት ከሚያሳዩ ሀገራት ተርታ ላይ አስቀምጧታል። የሀገሪቱም የአፍሪካ ቀንድ አቀማመጥ እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ ለተለያዩ የመካከለኛዉ ምስራቅ እና ሌሎችም የገበያ እድሎች ለዚህ እድገት ቀጣይነት ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።
ከዚህ ቀደም የነበሩቱ አብዛኛዎቹ የኢኮኖሚ እድገቶች በግብርና፣ ገጠር ልማት፣ መሰረተ ልማቶች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በአቅርቦቱ መስክ እና የግል እና የህዝብ ተጠቃሚዎች ደግሞ የፍላጎቱን መስክ እድገት ያሳያሉ።
መንግስትም የዕድገት ለዉጥ ትግበራዉን በማፍጠን እና ቀጣይነት ያለዉን እድገት በማስፋፋት በ 2035 እ.አ.አ ከመካከለኛ ዕድገት ላይ ካሉ ሀገራት ለማሰለፍ እየሰራ ይገኛል። ይሄንን እድገትም ለማፋጠን መንግስት መሰረተ ልማቶችን ከህዝብና ከግል ኢንቬስተሮችም ጋር በትብብር ጉዞዉን ጀምሮ ቆይቷል። አሁን ላይ ያለዉን የህዝብ ቁጥር ስናይ ወደ 120 ሚሊዮን ከሚጠጋዉ ህዝብ ትልቁን ድርሻ የያዘዉም ወጣቱ ሲሆን እነዚህም ከተሰራበት የህዝብ ቁጥሩም ሆነ የወጣቱ ቁጥር መልካም እድል የሚሆንበት ሁኔታ አለ። እነዚህ ሁሉ ወጣቶች፣ የጤና፣ የቤት፣ የትምህርት እና የስራ ዕድል ስለሚፈልጉ ይሄ ጫና የሚመስለዉን ጉዳይ ወደ እድል መለወጥ ተገቢ ነዉ።
ከሚሌኒዬሙ የእድገት እቅድ ኢትዮጵያ በ እናቶች እና ህጻናት ሞት ከፍተኛ መቀነስ ስራ ቢሰራም አሁንም ቢሆን ብዙ ስራ ይጠብቀናል። በቅርብ በወጣዉ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሰረት 60 በመቶ ሞት ከእናቶች ህጻናት እና ተላላፊ በሽታዎች ቢሆንም 30 በመቶዉ ደግሞ ከማይተላለፉ በሽታዎች ጋር ይያያዛል።
የትምህርት ጥራትንም ብናየዉ በጤናዉ ትምህርት ዘርፍ የጥራቱ ጉዳይም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። የትላልቅ ትምህርት ተቋማቶቻችንም ዉስጥ ገብተዉ በብዙ የሀገር ኢንቬስትሜንት የሚማሩ ምሁራንም የተሻለ ነገር ፍለጋ ከሃገር መሰደድ ላይ ይገኛሉ። ሀገር ዉስጥ የቀሩትም በህብረት ያላቸዉን እዉቀት፣ ጊዜ እና ገንዘብ አሰባስበዉ ወይም ከሌሎች ባለ ሃብቶች ጋር በህብረት በመሆን በሰፊዉ የመስራት ባህሉ ብዙም አይታይም።
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችን እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የተማሩ እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን የሆኑ ሰዎች በአንድነት በረጅም አመታት እቅድ ቢሰሩበት ፍሬያማ ዕዉቀት እና የስራ ዕድል ለወጣቱ፣ ለህብረተሰባችንም ደዌ መፍትሄ ብሎም በአንድነት እዉቀትን እና ገንዘብን አንድ ላይ ለሚሰሩበት ኢትዮጵያዉያን እርካታ፣ ክብር እና ሃብትንም ያጎናጽፋቸዋል።
በአንድነት ያለንን አሰባስበን መንግስትንም በጥናት በማሳመን መስተካከል ያለባቸዉን ጉዳዮች በማስተካከል ህዝባችንን ጠቅመን እኛም መጠቀም እንችላለን። በሀገራችን ያሉትን የመልካም አጋጣሚዎች መካከል፡-
የወደፊቱ የአለማችን ሀብት ምንጭ የሚባለዉ መረጃ ሲሆን በዚህ ላይ በሀገራችን እምብዛም አልተሰራም። ከላይ ያሉ የጤና ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት፣ ከመፍትሄዉ የሚገኘዉን ገቢ ለማግኘት እና ዉጭ ምንዛሬ ለማትረፍ የጤና ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶች ላይ መስራቱ ተቀዳሚ ነዉ። የጤናዉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት በሀገራችን ምንም ያልተሰራበት በሚባል ደረጃ ላይ ያለ ሲሆን አብዛኛዎቹም በዕርዳታ ድርጅቶች ላይ የተደገፉ ከመሆናቸዉም በላይ ዘላቂ የሆነ ሀገራዊ የጤና ቴክኖሎጂ ህልም ያላቸዉ ባለመሆናቸዉ የጤና መረጃዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል አልተቻለም። ስለዚህ በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን አለም አቀፍ የእውቀት አቅም ኖሯቸዉ ካልተጠቀሙ ኢትዮጵያዉያን ባለሙያዎች ጋር በመሆን መስራት የሚችሉበት መስክ ነዉ። በአንድነት ያላቸዉን በማሳየት መንግስትም ለዚህ ከመደበዉ በጀት ድጋፍ በማግኘት በቡድን ራስንም ሀገርንም መለወጥ ይቻላል።
አብዛኞቹ ህዝባችን የሚሞተዉ በጤና ግንዛቤ ማነስ እና የጤና አገልግሎት እጦት በመሆኑ የመረጃዉ ቴክኖሎጂ መኖር፣ ስራ አተዉ ያሉ የተማሩ ወጣት ሃይልን በመጠቀም እና በማሰልጠን፣ የስራዉም ሆነ የሃብቱ አካል በማድረግ በፒራሚዳል ስኪም ኢንሹራንም ሆነ መረጃን ማሰራጭት የሚቻልበትም ሁኔታ አለ።
የጤናዉን ትምህርት ብናይም አለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ የጤና ትምህርት መስጫ ተቋማት አንድም ያለመኖርን እንደ እድል በመቁጠር በጋራ በዚያም ዘርፍ ኢንቬስት በማድረግ መስራት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ አመቺ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል በሃገራችን ከፍያ እስኬል አለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑትን እና በተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የተማሩ ስፔሺያሊስት ሃኪሞቻችንን በአካል በኢትዮጵያ ሌሎችንም ደግሞ ካሉበት በ ቴክኖሎጂ በማሳተፍ የተማረ ሃይል በማምረት ለአለም አቀፍ ገበያ ማቅረብም ሆነ ለሀገር ማብቃትም ይቻላል።
አብረን በጋራ በመሆን ችግሮቻችንን በመጠቀም የመፍትሄም፣ የሃብትም ምንጭ እናድርጋቸዉ! የችግራችን ምንጭ አብሮ ያለመሮጥ፣ አብሮ ያለማሰብ ሲሆን፡ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ነዉና፤ ይብቃን አብረን አንሁን፣ አብረን እናስብ ያለንን አንስተን ችግር እንፍታ የመፍትሄም ምንጭ እናድረገዉ። ይሄ ስራ የሃብት ምንጭነት ብቻ ሳይሆን የዞሮ መግቢያችን ቤት ስራ ጉዳይ ስለሆነ እንበርታ።
ዋቢ ጽሁፎች
1. Ethiopia Growth and Transformation Plan II and Ministry of Health, Addis Ababa 2016: Investment Process in Ethiopia’s Health Sector. By National Planning Commission
2. Central Statistical Agency/CSA/Ethiopia and ICF. Ethiopia Demographic and Health Survey 2016. Addis Ababa, Ethiopia, and Rockville Maryland, US: CSA and ICF. 2016.
3. Health Systems 2020: Health Care Financing Reform in Ethiopia: Improving Quality and Equity.
https://www.hfgproject.org/wp-content/uploads/2015/02/Ethiopia_Health_Care_Reform_Brief1.pdf
4. Health Sector Development Programme IV, 2010/11–2014/15. Final draft (pdf 780.81kb). Addis Ababa, Government of Ethiopia, Federal Ministry of Health, 2010
በዶ/ር ተመስገን እንዳለዉ
(MD, Systems Developer, CSMM, MBA, MSc cand, CEO Hakim Consult)