ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ካልጀመርን ብለው ግብግብ ውስጥ የገቡት ሩሲያና አሜሪካ ዳፋው የሚተርፋቸው ሀገራት የሚያቀርቡትን የግልግል ኃሣብ የናቁ ይመስላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በዩክሬንና በሩሲያ መካከል ያለውን ፍጥጫ ለማስቆም እየሰራች የመሰለችው አሜሪካ አሁን ላይ በኔቶ ስም ካሰፈረችው ጦር በተጨማሪ የአሜሪካንን ሰንደቅ ብቻ የወከሉ ተዋጋ ሰርጓጅ መርከቦችን በመላክ ቀውሱን እያባባሰች ነው፡፡
የዚህ ማሣያው ደግሞ የዋሽንግተን ኒኩለር ተሸካሚ መርከቦች ረጅም ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የሩሲያን የባሕር ዳርቻ ሰብረው ገብተዋል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በባለ 4 ሜትር ርዝመት ጠረጴዛ የተወያዩት የፈረንሣዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዩክሬንን ለመውረር በሩሲያ በኩል ያየሁት ጠንካራ ዝግጅት የለም ብለው ተናገሩ፡፡ ይሁንና ይህንን ንግግራቸውን ያላመኑት የአሜሪካው አዛውንት ጆ ባይደን ወደ ሞስኮ ስልክ በመምታት ፑቲንን አነጋገሩ፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ በቆየው የሁለቱ መሪዎች ንግግር ግን ውጥረቱን ረገብ ሊያደርግ የሚችሉ ስምምነት ያልተደረሰበት መሆኑን አንድ የኋይት ሃውስ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡ የስልኩ ፍሬ አልባነትን ከሚጠቁሙ ጉዳዮች ደግሞ አንዱ ባይደን ለፑቲን የሰጧቸው ማስጠንቀቂያ ነው፡፡
የሞስኮ ጦር አሉ ባይደን የሞስኮ ጦር አሁን ካለበት ቦታ የተለያ እንቅስቃሴ ቢያደርግ ከምዕራቡ ጦር የሚኖረው ምላሽ የከፋ ነው፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሩሲያን ከዩክሬን እንለያያታለን ማለታቸውን ሬውተርስ አስነብቧል፡፡ ባይደን ይህንን ተናግረው ከወደ ፑቲን የሚመጣውን መልስ ሲጠባበቁ የሰሙትን ማመን አልቻሉም፡፡ በተረጋጋ መልኩ መልስ የሰጠት ፑቲን “አሜሪካ የሩሲያ ትኩረት መሆኗ ካበቃ ሰንብቷል” በዚህ መልስ የበገኑ የሚመስሉት ባይደን ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ ሳይጣስ ሰርጓጅ ተዋጊዎቻቸውን ወደ ሩሲያ ልከዋል፡፡ “ዩክሬንን ሊወር ነው” የተባው ጦር ከቦታው ሳይንቀሳቀስ የአሜሪካ የኒኩለር አረር ተሸካሚ ሰርጓጅ መርከቦች የሩሲያን የውሃ ክልል አልፈው መግባታቸው የተነገረው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሩሲያ የባሕር ኃይል በቨርጂኒያ 774 ኩሪል ደሴቶች በኩል ወደ ሞስኮ ሊገሰግሱ የነበሩ የአሜሪካ ተመሣሣይ መርከቦችን ከበባ ውስጥ አስገብቻለሁ ብሏል፡፡ እንደ ዘጋርዲያን ዘገባ ከሆነ ከዚህ ቀደም ሁለቱ ሀገራት ተመሣሣይ ክስተት ከገጠማቸው ለቀሽ ውጪ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰናዘሩ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህንን ማስጠንቀቂያ ትተው ምላሽ ለመስጠት ተሰናድተዋል፡፡ ሩሲያ ወደ እኔ ቀርቧል ላለችው የአሜሪካ ኃይል በሃይል እርምጃ ለማባረር በሚመስል መልኩ የምድር፣ የባህርና የአየር ኃይል ጦሯን ከፍተኛ በተባለ ንቅናቄ አስጠግታለች፡፡
ይህንን ያወቀው የአሜሪካ ኃይል የሩሲያን የውሃ ክልል ለቆ መውጣቱን ሬውተርስ ዘግይቶ ባወጣው መረጃ ላይ አስፍሯል፡፡ የአካባቢው ሁኔታ በዚህ መልኩ ሳይረግብ እያለ ንዝረቱ ዓለምን እያዳረሰ ይገኛል፡፡ ዋሽንግተን ደግሞ ሁኔታው በፍጥነት ቡድናዊ ቅርፅ እንዲይዝ ለማደረግ እየተሯሯጠች ነው፡፡ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንክን ከጃፓንና ደቡብ ኮሪያ መንግሥታት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መክረዋል፡፡
ከሩቅ ምሥራቅ ሀገራት በኩል የተባለ ነገር ባይገለፅም ብሊንከን ግን ቶኪዮና ሴኦል ከዋሽንግተን በኩል ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በርግጥ ከዚህ ንግግር አስቀድሞ ጃፓን በሥጋት ብቻ ወደ ሩሲያ መስመር የምታርጋቸውን አንዳንድ የንግድ ጉዞዎችን ሰርዛ ወደ ምዕራብ ሀገራት ማዞሯን በሣምንቱ መጀመሪያ አሳውቃ ነበር፡፡ አሁን ሀገራት ከየተኛው ወገን መሆናቸውን ለማሣየት በቡድናቸው የሚደረጉ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው፡፡ አውስትራሊያ የአሜሪካንን ጥሪ ተከትሎ ኬቭ ያሉ ዜጐቿን በአስቸኳይ ውጡ በማለት አዛለች፡፡
በዚህ ጥሪ በርከት ያሉ የአሜሪካ፣ የአውሮፓና አውስትራሊያ ዜጎች ኬቭን ለቀው እየወጡ ነው፡፡ አውሮፕላን አንጠብቅም ብለው ትዕግሥት ያጡ ሰዎች በመኪና ሲጓዙ አይቻለሁ ብሎ በኬቭ የሚገኘው የሬውተርስ ዘጋቢ ሁሜይራ ፓሙክ ዘግቧል፡፡ ሌላኛው የአሜሪካ ጥብቅ ወዳጅ እንግሊዝ በኬቭ ያሉ እንግሊዛውያን በሙሉ በፍጥነት ከዛ ቦታ ለቀው እንዲወጡና ወደዛ ሀገር በረራ ያላቸው ተጓዦች በረራቸውን እንዲሰርዙ አዘዋል፡፡
ካናዳ በበኩሏ በኬቭ ያለውን ኤምባሲዋን በመዝጋት በሌቪቭ ከተማ ጊዚያዊ የዲፕሎማቲክ ጉዳዮች ቢሮ አቋቁማለች፡፡ የካናዳ ውሣኔ ግን ጦርነቱ እንዲደረግ የፈለገች ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ሌቪቭ ከተማ የዩክሬን ዋነኛ ወታደራዊ ማዕከል ወይ ዕዝ መስጫ ቦታ በመሆኗ ነው፡፡ በተለይ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 ጦርነትን አስተናግደው ከ14 ሺ በላይ ሰዎች በሞቱባቸው ዶኔስክ እና ሉሀንስክ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የአሁኑም ውጥረት ወደ ግጭት ካመራ የጦር አውድማው ሊሆን የሚችለው ይኸው ደም የለመደው ቦታ ነው በሚል በፍጥነት እየወጡ ይገኛሉ፡፡
የአውስትራሊያው ጠ/ሚ/ር ስኮት ሞሪሰን ዜጎቻቸው ከመጣራት ባለፈው ለቻይናው መሪ ሺ ጂን ፒንግ ተማፅኖ መሰል ጥሪን አቅርበዋል፡፡ የፑቲን ወዳጅ ፒንግ በዚህ የዓለምን ዐይንና ጆሮ በሳበው ጉዳይ ላይ ዝምታን መምረጣቸው ልክ እንዳይደለ ኃሣባቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በቤጂንጉ የክረምት ኦሎምፒክ መክፈቻ ላይ የተገናኙት ሺ ጂን ፒንግና ቭላድሚር ፒቲን ገደብ አልባ ትብብር ለመከወን ከሥምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡
ሩሲያ በዩክሬን ላይ በምታደርገው ማንኛውም ዓይነት አድራጎት ቻይና ጣልቃ እንዳትገባና ሩሲያ በበኩሏ ቻይና በታይዋን ላይ በምትፈፅመው የትኛውንም ዓይነት ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት ወስነዋል፡፡ ይልቁኑ የጋራ ያሏቸውን የምዕራቡ ሀገራት መንግሥታትና የጣምራ ድርጅቶችን ጥቃት በጋራ ለመከላከል በሚል እጅ ለእጅ ተጨባብጠዋል፡፡ ፑቲን በየሄዱበት የሚያቀርቡት ቅድመ ሁኔታ አሁንም መልስ አላገኘም፡፡
ቤጂንግ በተገኙ ጊዜም አሜሪካና ኔቶ በዩክሬን የሚያደርጉትን መስፋፋት ያቁሙ፤ በተለይም ኔቶ ሚሳኤልን ጨምሮ በአውሮፓ የሚደረገው የጦር መሠረተ ልማት ዝርጋታ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1997 በነበረበት ልክ እንዲሆን የሚጠይቅ ነው፡፡ ታዲያ አሜሪካ ይህንን ሳትመልስ ነው ድርድር የምትፈልገው፡፡
ከነጩ ቤት የሚወጡት መረጃዎች መልካቸው ሁለትና ከዛ በላይ እይሆነ ነው፡፡ የአሶሼትድ ፕሬሶቹ ጂም ሔንዝ እና አሚር ማድሀኒ እንደሚሉት ባይደን በዚህ በጋለ የቃላት ውርወራ ውስጥም ቢሆን ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ አልረፈደም ማለታቸውን በዘገባቸው ውስጥ አካተዋል፡፡ እንደ ምንጮቹ ከሆነ ፑቲን በዩክሬን ላይ የሚያደርጉት ወረራ የቻይናው የክረምት ኦሎምፒክ እንስኪጠናቀቅ አይፈፀም ሲሉ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ጠቅሰው አውጥተዋል፡፡
ዘ ጋርዲያንና ሬውተርስም ይህ ልክ አይደለም ከአሜሪካ የጦር ሰላዮች አገኘነው ባሉት መረጃ መሠረት የሩሲያ ኃይል በመጪው ረቡዕ ዩክሬንን እንደሚወር አውቀናል ብለዋል፡፡ ፔንታገንም ይህንን ሊቀለብስ ያስችለኛል ብሎ ያሰበውን 3 ሺ ተጨማሪ ወታደሮችን ከፖላንድ በማንቀሳቀስ በጉዞ ላይ ያሉትን 1 ሺ 700 ወታደሮችን እንዲቀላቀሉ አዟል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የምዕራቡ ጥምር ጦር ጄቶች፣ መርከቦች፣ ተዋጊና ሰላይ ድሮኖች በሩሲያ የባህር አቅራቢያ ተደጋጋሚ ቅኝት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የሩሲያው መከላከያ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ ይህንን ትንኮሣ ያለማስጠንቀቂያ ያለፍነው በቂ ምላሽ የሚሰጥ ዝግጅት እያደረግን በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በርካቶች ቃላትን ሲወራወሩ በዝምታ የሚመርጡትና ዋነኛ የጉዳዩ ባለቤት የዩክሬን ፕሬዝዳት የሆኑት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አሌክሲ ሬዚንኮቭ እንዲሁም የጦር አዛዡ ሌ/ጀነራል ቫለሬቲ ዛሉዝኒ በጋራ አጭር መግለጫለ አውጥተዋል፡፡
የባሥልጣናቱ መግለጫ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገውን መራራ ጦርነትና ክሬሚያን ከዩክሬን ያስነጠቀውን ግጭት ወደ ኋላ ሄዶ የዳሰሰ ነበር፡፡ እኛ ከዛ መጥፎ ጠባሣ አገግመናል ፤ ምንም የሚያስፈራን ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር በቁጥጥራችን ሥር ነው በማለት ለሩሲያ መልስ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አውጀዋል፡፡
ጠላታችንን አበባ ይዘን አይደለም የምንቀበለው ያሉት ሦስቱ ባለስልጣናት የማይቀር ለሚመስለው ፍልሚያ ሩሲያ ለትምልከው ተዋጊ በሙሉ ፀር በመሆን የሲኦል ሽኝት እናደርግላታለን ብለዋል፡፡ ወራትን በዲፕሎማሲያዊ ንግግሮች፣ በዛቻና ማስፈራራት የሰነበተው የሁለቱ ሀገራት ጉዳይ ወደ ግጭት ካመራ የሚፈጠረው ሰብዓዊ ውድመትና የምጣኔ-ሐብት ኪሣራ አንፃር በደንብ አልታየም ይላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፡፡
የመሣሪያ ድምፅ ያልነበረው የአሜሪካና ቻይና የንግድ ጦርነት ዓለም ላይ በፉክክሩ ቀለበት ውስጥ ያልነበሩ በርካታ ሀገራትን በቀጥታ ጐድቶ እንደነበር የአልጀዚራ ዘገባ አስታውሷል፡፡ የአሁኑ ውጥረት ወደ ግጭት ካመራ ቻይናም ምላሽ መስጠቷ አይቀርም ባንድም ይሁን በሌላ፡፡ ይህ ደግሞ በዓለማችን ምጣኔ-ሐብት ላይ የሚያስከትለው ጫና ከባድ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን በመሰሉና ቀድሞውኑ በጦርነትና በማዕቀብ ምጣኔ-ሐብታቸው ለተጎዳባቸው ሀገራት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ትንታኔ ዘገባውን ስናዘጋጅ በዋቢነት አሶሼትድ ፕሬስ፣ ሬውተርስ፣ ዘጋርዲያንና አልጀዚራን ተጠቅመናል፡፡
በዘመድኩን ብሩ