ጥቂት የመልካምነት ጠብታዎች ተጠራቅመው ትልቁን የሰብአዊነት ባህር ይሰራሉ፡፡ መልካም ዛፍ መልካም ፍሬን ታፈራለች የሰው ልብም የመልካም ቡቃያ አውድ ናት፡፡ እኛም ከፈጣሪ የተሰጠንን ብዙ መልካም ነገሮች ውስጥ ጥቂቷን መልካምነት አጠገባችን ላሉት ሰዎች እናካፍል የሰው ልጅ መልካም ነገር ቢያደርግ ብዙ ነገሮችን ያተርፋል መልካም ስራ የክፉ ቀን ስንቅናትና፡፡
ስለዚህ ጥሩ ነገር በመስራት ለህሊናችን ሀሴትን እናቀብል፡፡ እኛም በመልካምነትና በጥሩነት ትልቅ ልንሆን ይገባል ትልቅነት የሚመጣው ከትልልቅ ሀሳቦች ነው፡፡ ሀገርም የአስተሳሰብና የመልካም ሀሳብ ውጤት ናት፡፡ ነገሮች በመልካም አስተሳሰቦችና ሀሳቦች ይደራጃሉ፡፡ ሀገርም የሚገነባው በጥሩ ሀሳብ ነውና፡፡ ሀሳብና አመለካከታችንን ወደ ጥሩና መልካም ነገር ከቀየርን የማንለውጠው ነገር የለም፡፡ አሁንም ካለንበት ችግር ለመውጣት መፍትሄው ያለው በእያንዳንዳችን መዳፍ ላይ ነው፡፡ ነገሮችን ለመቀየር እያንዳንዳችን የመፍትሄ ሀሳብ ልናዋጣ ይገባል፡፡
በመጀመሪያ የተቸገርነው ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ከዚያም ችግሮችን ለመፍታት እና ለመግታት የእኔ አስተዋፅ ምንድን ነው ብሎ ራስን መጠየቅ ሁሌም ወደ መልካም አስተሳሰብ እናዘንብል፡፡ አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ ማተኮር አንድነትና የጠነከረ ወዳጅነት ይፈጥራልና፡፡
ሁሌም ቢሆን ለአምሮአችን መልካም መልካሙን ጥሩ ጥሩውን ልናሳስበው ይገባል፡፡ ምክንያቱም አእምሮአችን የሰጠነውን ይቀበላልና፡፡
ወደኋላ መለስ ብለን የእናት አባቶቻችንን ጥበብ እንመልከት እንዴት አድርገው ወዳጅነታቸውን እንዳጠነከሩ እንዴት መተባበርና ችግርን መሻገር እንደቻሉ እንዴት ሀገርን በነፃነት ማስቀጠል እንደቻሉ፡፡ እናስታውስ
አሁን ደግሞ ከምንጊዜውም በላይ በብዙ ነገር ልንጣመር ልንዛመድ ይገባል፡፡ የበለጠ ደግሞ ልንወዳጅና ልንረዳዳ ያስፈልጋል፡፡ በከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን እናስብ እናስታውስ ለሀገራችን የተዋደቁትን ሰማህታት በህሊናችን እናመላልስ አሁን መርጠን የምንበላበት ተሽቀርቅረን የምንወጣበት ጊዜ አይደለም፡፡ አሁን የምንጨፍርበት የመዝናናት ጊዜ ላይ አይደለንም ይልቁኑ ነገሮችን በጥሞና የምንመለከትበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ ብዙ ነፍስ ለኢትዮጵ ለህዝቦቿ ለእኛና ለእናንተ ተርበዋል፣ ተራቁተዋል ተሰደዋ፣ ብዙ ችግሮችን አይተዋል ክቡር የሆነውንንም ሂወታቸውንም ከፍሏል፡፡
ስለዚህ በተከፈለልን ዋጋ ነው የቆምነው፤፤ ይህን ደግሞ ከየትኛውም ጥግ ያለ ኢትዮጵዊ ሊያውቀውና ሊረዳው ይገባል፡፡ የሰላም እንቅልፍ የሰላም አየር መተንፈስ በሰላም ወጥቶ መግባቱ እንዲሁ በቀላሉ የመጣ አይደለም፡፡ ሰላማችን የመጣው ሀገር ወዳድ ጀግኖች በከፈሉት መሰዋትነት ነው፡፡ እነዚህን ሰማህታት ደግሞ ዋጋ ልናሳጣ አይገባም፡፡ ከቻልን የምንችለውን እናድርግ አጠገባችን ያሉትን ሰዎች እንመልከት ወገኖቻችንን እንመልከት ጦርነቱ በነበረበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ያላቸውን ችግር እንካፈላቸው፡፡ ሁሉም የአቅሙን ያድርግ፡፡ ለመልካምነት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡
ስለዚህ ለጊዜው ደስታና ጭፈራው ሆያሆዬውን ቆም አድርገን ለተቸገሩ ወገኖቻችን እንድረስላቸው እናስታውሳቸው ካልሆነ ግን “የአንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” ነውና ነገሩ “ነግ በኔ” እናስብ፡፡ ከዚህ ምድር መች እንደምንሰናበት እንኳን የማናውቅ ፍጡሮች የሰው ህመም ሊያመን ይገባል፡፡ ሁሉ ነገር በልክ ይሁን አይናችንን እና ጆሮአችንን እነዛ ለኢትዮጵያ ሲሉ ለተዋደቁ እና ለተቸገሩ ለተሰደዱ ወገኖቻችን እናውሳቸው፡፡
በተቻለን አቅም የሚጠበቅብንን እናድርግ ይህ ከሆነ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቀርብ ነው፡፡ እንተባበር እንተጋገዝ እንጎራረስ እንተሳሰብ የዚያን ጊዜ አንድነቱ ይመጣል፡፡ ልዩነታችንን አርግፈን እንጣል አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ላይ እናትኩሩ አንድ ስንሆን ማንም አይራብም፣ ማንም አይጠማም ማንም አይራቆትም፡፡
አንድ ስንሆን ለአለም የተረፍን ህዝቦችን እንደነበርን የዓለም የታሪክ መዛግብት ምስክሮች ናቸው፡፡
በመጨረሻም አንድነታችንን እናጠናክር ለመረዳዳት እና ለማገዝ ዝግጁ እንሁን ጠንክሮ ለመስራት ወገባችንን ታጥቀን እንነሳ፤፤
ይህ ከሆነ ሁሉም ቀና ይሆናል ግድ የለም መልካምና ጥሩ ቀን ይመጣል የክፋት በሮች ሁሉ ይዘጋሉ ለቅሶና ዋይታም ይቆማሉ ስጋትና ፍርሀትም ይጠፋሉ በምትኩም ሀሴትና ደስታ ተስፋና ብልፅግና ሰላምና መረጋጋት ለኢትዮጵያ ይሆናል፡፡
ቤንኦን ጌታቸው።
15/05/2014 ዓ.ም