“የባህል ወረራን የሚዋጋ ማኅበረሰብን ለመገንባት ባህልን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል…”
አቶ አህመድ ዘከርያ – የታሪክ እና ባህል ጥናት ተመራማሪ
ማኅበረሰብ በመኖር መስተጋብር ውስጥ የሚፈጥራቸው ልምዶች በጊዜ ሂደት ወደ ባህልነት ያድጋሉ፡፡ ይህ ማኅበረሰባዊ ልማድ በጊዜ ዑድት ውስጥ የሚያድግ ፤ ከአንዱ ማኅበረሰብ ወደ ሌላ ማኅበረሰብ የሚወራረስ እንደ ሆነ ሁሉ በትውልድ ቅይይር ውስጥ ማኅበረሰብ ካለው ባህል ላይ የሚጠቅመውን እያነሳ እና ጎድቶኛል ያለውን እየጣለ ይሄዳል፡፡
ባህል ያልተፃፈ ግን ማኅበረሰቡ በስምምነት ያወጣው ሕግ ነው፡፡ ባህል የአንድ ማህበረሰብ መገላጫም ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ኃይል ሳትገዛ የኖረች አገር መሆንዋ ማኅበረሰቡ የራሱን ቀለም ሳይለቅ ባህሉን ጠብቆ እንዲኖር አድርጓል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉ በርካታ ቋንቋ ያላቸው አገራት እንደ ኑሮ ዘያቸው መለያየት የሚገነቡት በርካታ ባህል አለ፡፡ ታድያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ነባር የነበሩ የመከባበር፣ የመደማመጥ እና የእርቅ እሴቶቻችን እየተሸረሸሩ ግጭት የነገሰበት መደማመጥ ያቃተው፣ መከባበር የተሳነው ማኅበረሰብ መታየት ጀምሯል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ሰፊ የባህል ወረራ ስለመኖሩ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ዓለም ወደ አንድ መንደር መሰብሰብ መጀመሯና የቴክኖሎጂ መስፋፋት ለዚህ የባህል ወረራ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ፊልሞች ፣ የሙዚቃ ክሊፖች እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚታዩ ክዋኔዎች በታዳጊ ወጣቶች ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ይኸው የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ለባህል ወረራ መስፋፋት ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የዓለም ወደ አንድ መንደር መምጣትዋን ተከትሎ ይህንኑ ግንኙት የሚያጠናክር ቴክኖሎጂም እለት እለት እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ በአገራችን ለሚታየው የባህል ወረራ ይህንኑ የቴክኖሎጂ ግንኙነት መጠናከር መስፋፋት ተጠያቂ የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ ጥበቡ በለጠ በዚህ ኃሳብ አይስማሙም፡፡
“በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው የባህል ወረራ መሠረታዊ ችግሩ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ መምጣት አይደለም፡፡ ችግሩ ለማኅበረሰቡ ቀደሞ ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀም ግንዛቤ ካለመፈጠሩ ጋር የተያያዘ ነው” ይላሉ አቶ ጥበቡ ፡፡
በ2006 ዓ.ም በባህል ወረራ ላይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ደረጃ ጥናት እንደተደረገ የሚያነሱት የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አለማየሁ ጌታቸው ለባህል ወረራው የመገናኛ ብዙሃኑ እና የመዝናኛው ኢንዱስትሪ ትልቅ አስተዋፅዖ እንዳለው ያነሳሉ፡፡
ባለፉት ጊዜያት በኢትዮጵያ የነበረው ፖለቲካ ስርዓት በአገራዊ ፍልስፍና ላይ የተመሠረተ አለመሆኑ አገራዊ እሴቶች ጠባቂ አልባ ሆንዋል ሲሉም ከዚህ ቀደም የነበረው የፖለቲካ ስርዓት ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡
በ1950ዎቹ መጨረሻ ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት በኢትዮጵያ ሲመሠረት ከዚህ ቀደም የነበረውን አገራዊ እሴቶች ማስቀጠል አልቻለም የሚሉት አቶ አለማየሁ “የራስን ጥሎ የሰውን አንጠልጥሎ” ይሉት የፖለቲካ ባህል ዳብሮ መቆየቱን ያነሳሉ፡፡
በዘመናዊው የፖለቲካ ስርዓት ቀደምት የኢትዮጵያ እሴት የነበሩ ልማዶች እንደ ኋላ ቀር እና የማይጠቀሙ ተደርገው መሳላቸው አሁን ለደርስንበት የባህል ውዥንብር አጋልጦናል ብለው አንደሚያምኑ አንስተዋል፡፡
የአቶ አለማየሁን ኃሳብ የሚጋሩት አቶ ጥበቡ ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ የነበረው የፖለቲካ ስሪት ጥላቻን የሚሰብክ እና ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚያዳክም መሆኑ ለትውልድ ስብራት ዳርጎናል ይላሉ፡፡ የማኅበረሰቡ የንባብ እና የውይይት ባህል ሊያድግ አለመቻሉ አሁን ለሚታየው የባህል መደበላለቅ እንደዳረገን ጨምረው አንስተዋል፡፡
ዛሬ በአገራችን የሚታየው ግጭት እና አለመግባባት የባህል ወረራው ውጤት ነው የሚሉት የታሪክ እና ባህል ጥናት ተመራማሪው አቶ አህመድ ዘከርያ ናቸው፡፡
የባህል ወረራን የሚዋጋ ማኅበረሰብን ለመገንባት ባህልን ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል የሚሉት ተመራማሪው ማኅበረሰብን ስለ እሴቶቹ ጠንቅቆ እንዲያውቅ ማድረግ ላይ በትኩረት መሠራት አንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት የባህል ወረራ ችግሮችን በመለየት የመከላከያ ስልት ነድፎ ሲሰራ መቆየቱን ያነሱት አቶ አለማየሁ የባህል ወረራን በመከላከል እረገድ የወጡ ሕጎች ቢኖሩም የወጡትን ሕጎች ማስፈጸም ላይ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸውን አልሸሸጉም፡፡
ጨምረውም የባህል ወረራን መከላከል ለአንድ ተቋም የሚተው ሥራ አይደለም የሚሉት አቶ አለማየሁ ሁሉም ዜጋ በአካባቢው የሚመለከታቸው መጤ ተግባራት በመዋጋት የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት እንዳለበት አንስተዋል፡፡
መጤ ባህልን በመዋጋት ረገድ የተለያዩ የሙያ ማህበራት የራሳቸውን አስተዋፅዖ ማበርከት እንደሚገባቸውም አቶ አለማየሁ ጨምረው አንስተዋል፡፡
የዘገበው፡- ይስሃቅ አበበ