ለሀገር ውስጥ የሚቀርብ የቡና ዋጋ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ጨምሯል።
ለሀገር ውስጥ የሚቀርብ የቡና ዋጋ ከወትሮ በተለየ ሁኔታ ለየት ብሎና በተጋነነ መልኩ እንደየ ቡናው ደረጃ በአንድ ኪሎ ከ80 ብር እስከ 200 ብር የሚደርስ ጭማሪ እየተስተዋለ ይገኛል፡፡
አዋሽ ሬድዮ በአዲስ አበባ ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ቅኝት የአንድ ሲኒ ቡና ከ7 ብር እስከ 15 ብር ይሸጥ የነበረው ዋጋ አሁን ላይ አንድ ሲኒ ቡና ከ20 ብር በላይ እየተሸጠ እንደሆነም ለማየት ችሏል፡፡
ኢትዮጵያ የታወቀችበት የኮፊ አረቢካ ቡና እስከ ደረጃ 5 የሚሆነው ለዓለም ገበያ የሚቀርብ ሲሆን ከዚያ በታች ያለው ቡና ግን ለሀገር ውስጥ ገበያ የሚውል ነው፡፡
ኢትዮጵያ በየዕለቱ ከ1 ሺ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ ሀገራት እየላከች መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡
ለዓለም ገበያ ከሚቀርቡ የቡና ደረጃዎች በተጨማሪ ከደረጃ 5 በታች ያሉ የቡና ዓይነቶች በአሁኑ ሰዓት ተፈላጊነታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡
ብራዚል በገጠማት የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ቡናን ለዓለም ገበያ በሚፈለገው ልክ እያቀረበች አለመሆኑ ሌሎች የቡና አምራች ሀገራቶች ኢትዮጵያን ጨምሮ የቡና ዋጋቸው እንዲጨምር አድርጎታል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራአስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ የአለም አቀፍ የቡና ገበያ ሲጨምር ሀገር ውስጥ ያሉ ቡናን ወደ ውጭ የሚለኩ ነጋዴዎች በተሻለ ዋጋ ገዝተው ይሸጣሉ፤ ስለዚህም ነው የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ የጨመረው ይላሉ፡፡
አቶ ግዛት የቡና አቅራቢዎችና የቡና ላኪዎች ተገናኝተው የሚገበያዩበት ቦታ የላቸውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ነፃነት ተስፋዬ ግብይቱን የሚፈፅሙ ነጋዴዎችና ማኅበራቶች ለተቋማችን ቡና ያቀርባሉ ፤ ደረጃ ከተሰጣቸው በኋላ በእኛ የምርት ገበያ በኩል መድረክ ላይ በሚደረግ ግብይት ለላኪዎች ይሸጣሉ፡፡
ይህም የሚሆነው ለኢትዮጵያ የቡና ግብይት እድገት ከተቀመጡ አማራጭ የግብይት ዘዴዎች አንዱ ነው ሱሉ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና የግብይት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር የቡና ዋጋ መጨመር በዓለም ደረጃ እንደሆነ ገልፀው በኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የቡና ዋጋ መጨመሩ አርሶአደሮቹም የሀገር ውስጥ ምጣኔ-ሐብቱም እንዲያድግ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
አቶ ሻፊ በሀገር ውስጥ የተፈጠረውን የቡና ችግር ለመቅረፍ ያለውን ተረፈ ምርት ጊዜና ሰዓቱን ጠብቆ ወደ ገበያ በማውጣትና ተረፈ ምርቱ እንዴት መሆን አለበት በሚል የተቀመጡ አዋጆችና መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ባሳለፍው የ2013 የበጀት ዓመት ወደ ውጭ ሀገር ከተላከ ቡና 907 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡
ባለሥልጣኑ በያዝነው የ2014 በጀት ዓመት 280 ሺ ቶን ቡና ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ ያቀደ ሲሆን በበጀት ዓመቱም 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እንደታቀደም ገልጿል፡፡
በዳኛቸው መላኩ